አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ ክልል መንግስት ለወጣቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰራ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ።
የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በአዳማ ከተማ በወቅታዊ ጉዳዮች እና በሀገራዊ ለውጡ ዙሪያ ለወጣቶች ሲሰጥ በነበረ ስልጠና ላይ ተገኝተው ለተሳታፊዎች ቀጣይ የስራ አቅጣጫ ሰጥተዋል።
አቶ ሽመልስ በስልጠና መድረኩ መዝጊያ ላይ ባደረጉት ንግግርም፥ ከወጣቶች ጋር በጋራ መስራት ፈተናዎችን በቀላሉ ለማለፍ እንደሚያስችል ገልፀዋል።
ወጣቶችም መንግስት የሚሰጣቸውን ልዩ ትኩረት ከግምት ውስጥ በማስገባት ትክክለኛ አቋም ሊኖራቸው ይገባል ያሉት ርእስ መስተዳድሩ፥ በገንዘብ ከሚደለሉት ጋር መቀላቀል እንደሌለባቸውም አውስተዋል።
ለኦሮሚያ የሚገባትን እና መስራት ያለብንን ነገር ማሳየት ያለብንም በስራ እንጂ በማህበራዊ ትስስር ድረ ገፅ አይደለም ሲሉም አቶ ሽመልስ ተናግረዋል።
ርእስ መስተዳድሩ በንግግራቸው፥ ኦሮሚያን መገንባት ግዳጃችን ነው፤ በዚህ ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያን የመደገፍ እድል ይኖራታል ብለዋል።
በስልጠናው ላይ የተሳተፉ ወጣቶች በበኩላቸው አሁን ያለው ሁኔታ አንድ ወጣት ለሀገሩ እንዲያኖር የሚጠበቅበትን አሻራ ለማኖር አመቺ መሆኑን በመግለፅ፤ አንድ መሆን እና መስራት ያለብን ጊዜ አሁን ነው ብለዋል።
በኢዶሳ አብዲ
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

