አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 5 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ያልደረሳቸው ትምህርት ቤቶች ጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም ትምህርት እንዳይጀምሩ ትምህርት ሚኒስቴር አሳሰበ።
የትምህርት ሚኒስቴር በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ያስመረተውን የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ተረክቧል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያም የተረከቡትን ጭምብል ለክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎችና ተወካዮች አስረክበዋል።
በወረዳና ከዚያ በታች ያሉ ትምህርት ቤቶች ጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም ትምህርት እንዲጀምሩ ይደረጋል ያሉት ሚኒስትሩ ÷ በቦታዎች ርቀትና በተለያዩ ምክንያቶች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ያልደረሳቸው ትምህርት ቤቶች ትምህርት እንዳይጀምሩ አሳስበዋል።
ሌሎች ዝግጅቶች እንደተጠበቁ ሆነው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንደደረሳቸው ግን ትምህርት መጀመር ይችላሉ ብለዋል።
እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ሁሉንም ትምህርት ቤቶች ትምህርት ለማስጀመር የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከተቀመጡት መስፈርቶች ውስጥ አንዱ የሆነው የማስክ አቅርቦት ስራ በሁሉም ትምህርት ቤቶች እየተከናወነ ነው።
በሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተመረተውን ማስክም ወደየ ትምህርት ቤቶች የማድረስ ስራ እየተሰራ ነው ተብሏል።
የትምህርት ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና የኢንዱስትሪ ፓርክ ኃላፊዎችን ጨምሮ በዚህ ስራ ለተሳተፉት ሁሉ ምስጋና ማቅረባቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

