አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ ያለውን የተፈጥሮ ጋዝና ድፍድፍ ነዳጅ አቅም በሚፈለገው ልክ ለመጠቀም እንደሚሰራ የማዕድንና ነዳጅ ሚንስቴር ገልጿል።
ሚንስቴሩ ይህንን ያለው በዛሬው ዕለት በሶማሌ ክልል የሚገኙ የካሉብና ኢላላ የተፈጥሮ ጋዝና የድፍድፍ ነዳጅ ማውጫ ፕሮጀክቶች ያሉበትን ሁኔታ በተጎበኘበት ወቅት ነው።
ፕሮጀክቶቹን የማዕድና ነዳጅ ሚንስትሩ ኢንጅነር ታከለ ኡማ፣ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ ከሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር በመሆን ነው የጎበኙት።
ኢንጅነር ታከለ ኡማ አሁን ላይ በሶማሌ ክልል የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝን በዋናነት ገበያ የማፈላለግ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በድፍድፍ ነዳጅ ግኝት፣ጥናትናየዘርፉን ልማት በሚገባው ልክ ለማሳደግም መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን ላይም በሶማሌ ክልል ያሉትን የድፍድፍ ነዳጅ ፕሮጀክቶች በሙሉ አቅም ለማንቀሳቀስ ከፖሊጂሲል ኩባንያ ጋር በቅርበት ይሰራል ብለዋል።
ኩባንያው በሙሉ አቅሙ እንዲሰራም ይደረጋል ነው ያሉት ኢንጅነር ታከለ ኡማ።
በተጨማሪም የማዕድንና ነዳጅን የማልማት ስራ የአንድ ትውልድ ተግባር ስላልሆነ ይህ ትውልድ የዘርፉን መሰረት ለመጣል ስራ ይሰራል ሲሉም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በእስካሁኑ ሂደት 6 ነጥብ 4 ትሪሊየን ኪዩቢክ ፊት የተፈጥሮ ጋዝ በጥናት ተለይቷል።
ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ በቀጣይም ወደ ሌሎች ክልሎች በመሄድ በዘርፉ ላይ ያሉትን ችግሮች የመለየትና አፋጣኝ መፍትሄ ለመስጠት ይሰራል ተብሏል።
የመንግስትም ትኩረት በሃገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ውስጥ የማዕድና ነዳጅ ዘርፉ የዋነኛ የምጣኔ ሃብቱ ምሰሶ እንዲሆን ማድረግ ነው ተብሏል።
በምስክር ስናፍቅ
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

