Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከዲክኒል ዳጉሩ የሚገኘውን 80 ኪሎ ሜትር መንገድ ለማሻሻል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያና ጂቡቲ የጋላፊ ጅቡቲ መንገድ አካል የሆነውን የዲክኒል ዳጉሩ 80 ኪሎ ሜትር መንገድን ለማሻሻል ስምምነት ተፈረመ፡፡
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው እና የጂቡቲ ወደብ ኮሪደር መንገዶች ዋና ዳይሬክተር አብዲ ኢብራሂም ፋራህ ተፈራርመውታል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ ከኢትዮጵያ ድንበር እስከ ጂቡቲ ወደብ ከሚገኘው 220 ኪሎ ሜትር መንገድ ውስጥ ከዲክኒል እስከ ዳጉሩ የሚገኘው 80 ኪሎ ሜትር መንገድ በጣም የተጎዳና ለትራንስፖርት እጅግ በጣም አስቸጋሪ መሆኑ ይነገራል፡፡
በዚህ ሳቢያም ከጂቡቲ ወደብ ወደ ኢትዮጵያ የሚደረገው ጉዞ በጣም አስቸጋሪ፣ የተራዘመ ጊዜ የሚወስድና ተሽከርካሪዎች በተደጋጋሚ እንዲጎዱ የሚያደርግና ለአደጋ የሚያጋልጥ ጭምር ነው ተብሏል።
በፊርማ ስነስርአቱ ላይ የኢትዮጵያ ትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ እና የጅቡቲ ወደብ ነጻ ቀጠና ባለስልጣን አቶ አቡበከር ኡመር ሀጂ ተገኝተው ሁለቱን ወገኖች አፈራርመዋል፡፡
ከዲክኒል ዳጉሩ የሚገኘው 80 ኪሎ ሜትር ተለዋጭ መንገድ ጥገና እና መልሶ ግንባታ ወዲያውኑ የሚጀመር ሆኖ የዋናው መንገድ ግንባታ በቀጣይ ሁለት ወራት ውስጥ እንደሚጀመር በስምምነቱ ወቅት መገለጹን ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
Exit mobile version