አዲስ አበባ ፣ጥቅምት 5 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዳዋ ጨፋ ወረዳ ከ9 ሚሊየን 700 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው የኮንትሮባንድ እቃ ዛሬ መያዙን በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የኮምቦልቻ ቅርንጫፍ አስታወቀ።
የቅርንጫፉ ደንበኞች ትምህርት ቡድን አስተባባሪ አቶ አሳምነው አዳነ ÷ ልባሽ ጨርቃጨርቅ የሆነው ይሄው እቃ በቁጥጥር ስር የዋለው በህብረተሰቡ ጥቆማ መሆኑን ገልጸዋል።
ከባድ የጭነት ተሽከርካሪ በኮንቴይነር ሙሉ ብዛት ባላቸው ቦንዳዎች የታጨቁ ልባሽ ጨርቃ ጨርቆች ጭኖ ከደሴ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዳዋ ጨፋ ወረዳ ገርቢ ቀበሌ እንደደረሰ በቁጥጥር ስራ ማዋል መቻሉን አስረድተዋል።
አሽከርካሪው በቁጥጥር ስር ውሎ ጉዳዩ በህግ እየተጣራ መሆኑንም አመልክተዋል።
ጥቆማው እንደደረሳቸው የፌደራልና መደበኛ ፖሊስ እንዲሁም የጉምሩክ ባለሙያዎች ባደረጉት የተቀናጀ ጥረት እቃውን በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን አቶ አሳምነው ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

