አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ለቱሉ ሞዬ የእንፋሎት ሀይል ማመንጫ 1 ነጥብ 55 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ።
የኮርፖሬሽኑ ድጋፍ የቱሉ ሞዬ የእንፋሎት ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክትን የልማት ሂደት ለመደገፍ እና 50 ሜጋ ዋት ሀይል ማመንጨት የሚያስችለውን ዲዛይን ስራ ለማፋጠን ያስችላል ነው የተባለው ።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በኢትዮጵያ ትልቁ የእንፋሎት ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት እንደሚሆን ይጠበቃል።
የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ከልማት መሳሪያዎቹ አንዱ የሆነውን የቴክኒክ ድጋፍ በመጠቀም የዲዛይን ስራውን ይደግፋል ብለዋል የተቋሙ ዋና ባለሙያ አዳም ቦኤህሌር።
ዋና ባለሙያው ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ወሳኝ ሀብቶቿን ለኢኮኖሚ እድገቷ እንድትጠቀምበት ያስችላልም ነው ያሉት።
ቱሉ ሞዬ የእንፋሎት ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በአራት ዙሮች የሚገነባ ሲሆን፥ አሁን ድጋፍ የተደረገለት የመጀመሪያው ዙር ሲሆን 50 ሜጋ ዋት ሃይል ያመነጫል፡፡
አጠቃላይ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅም 520 ሜጋ ዋት ሃይል ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ነው እየተከናወነ ያለው፡፡
ምንጭ፥ thinkgeoenergy.com

