አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኮቪድ 19 ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ትምህርት ለማስጀመር የተቋማቱን ዝግጅት የተመለከተ የመጨረሻ ግምገማ እየተደረገ ነው።
የግምገማው አላማ የኮሮና ቫይረስን እየተከላከሉ መደበኛውን ትምህርትና ስልጠና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማስቀጠል ነው ተብሏል።
በግምገማ መድረኩ የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ፣ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ የግል እና የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዚዳንቶች፣ የቦርድ ሰብሳቢዎች፣ የሰላምና ጸጥታ ተቋማት ተወካዮች እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ እንዳሉት ከፍተኛ የትምህርትና ስልጠና ተቋማት ሰላማዊ እና የተረጋጋ አሰራር መፍጠር እንዲችሉ የሚመለከታቸው አካላት ሊያግዟቸው ይገባል።
የሳይንስ እና ከፍተኛ የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ በበኩላቸው የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማቱ ሰላማዊ እና ጤናማ እንዲሆኑ ከተለመደው አሰራር ወጣ ባለ መልኩ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የትምህርት ተቋማቱ የፈጠራ እና እውቀት ማእከል እንጂ የጫጫታ፣ የሁከት እና ግጭት መፈጠሪያ መሆናቸው ሊያበቃ ይገባልም ብለዋል።
በይስማው አደራው

