አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 9 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ በ4 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ሰባት አዳሪ ትምህርት ቤቶችን እና 100 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለማስገንባት የሚያስችለውን ስምምነት ከተቋራጮች ጋር ተፈራርሟል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ÷ የክልሉ መንግስት ዘንድሮ ለግንባታው 4 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር መመደቡን ተናግረዋል።
ይህም የፕሮጀክቶቹ ግንባታ በእውቀት የተገነባ ትውልድን ለመፍጠር የሚያግዝ ነው ብለዋል።
በፊርማ ስነ ስርቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ÷ የፕሮጀክቶቹ ግንባታ ከ ሰባት እስከ ስምንት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ዝግጁ እንዲሆኑ ተቋራጮቹ የገቡትን ውል እንዲፈጽሙ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ ርዕሰ መስተዳድሩ በግል ጥረታቸው ከውጭ ሀገር የሰበሰቡትን 210 ኮምፒውተሮች ለሰባት ትምህርት ቤቶች አስረክበዋል።

