አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 10 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ወባን ማጥፋት ከእኔ ይጀምራል በሚል መሪ ቃል የወባ ሳምንት እየተከበረ ነው፡፡
ሳምንቱ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥቅምት 27 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ነው የሚከበረው፡፡
የወባ ሳምንቱን አስመልክቶ የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴና የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማህተመ ሀይሌ እንዲሁም የዞን ጤና መምሪያ ሀላፊዎች በተገኙበት ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡
የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲቲዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ማህተመ ሀይሌ የወባ ስርጭት ካለፈው ተመሳሳይ ሩብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር አራት በመቶ መጨመሩን ተናግረዋል::
በዚህም ባለፈው ዓመት ሶሰት ወራት 122 ሺህ 747 ሰዎች በወባ ሲያዙ በተያዘው ዓመት ሶሰት ወራት ደግሞ 127 ሺህ 595 ሰዎች ተይዘዋል ነው ያሉት፡፡
የክልሉ የጤና ቢሮ ሀላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ በበኩላቸው የ99 በመቶ የወባ ህሙማን መመሪያው በሚያዘው መሰረት በላቦራቶሪ ተረጋግጦ የወባ መድሃኒት እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም የወባ ስርጭትን ለመከላከልናለመቆጣጠር ጤና ቢሮው ከክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲቲዩት ጋር በቅንጀት ህዝብን ባሳተፈ መልኩ እየሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
በናትናኤል ጥጋቡ

