አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ብሪታንያ በአውሮፕላን ማረፊያዎች ውስጥ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ መጀመሯ ተነግሯል።
በዛሬው እለት ከለንደን ሂትሮ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ሆንግ ኮንግ በረራ ያደረጉ መንገደኞች ፈጣን የኮሮና ቫይረስ ምርመራ አገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውም ተነግሯል።
በአውሮፕላን ማረፊያው ውስጥ የሚደረገው ምርመራ 89 ፓውንድ የሚያስከፍል ሲሆን፥ ውጤቱም በአንድ ሰዓት ውስጥ የሚደርስ ነው ተብሏል።
የምርመራው ዋነኛ ዓላማ በመዳረሻ ላይ የኮሮና ቫይረስ የምርመራ ውጤት የሚጠየቁ መንገደኞችን ለማገዝ መሆኑም ነው የተነገረው፡፡
በአውሮፕላን ማረፊያ ተርሚናል የኮሮና ቫይረስ ምርመራውን የጀመረው ኮሊሰን የተባለ ኩባንያ እንደሆነም ተነግሯል።
ኩባንያው ይህንን ፈጣን የመንገደኞች ምርመራ በጣሊያንም ለመጀመር እንዳቀደ እና በአሁኑ ወቅትም ከሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋር እየተነጋገረ መሆኑም ተገልጿል።
በርካታ ሀገራት መንገደኞች ድንበራቸውን ከመሻገራቸው በፊት 72 ሰዓት ያልሞላው የኮሮና ቫይረስ የምርመራ ውጤት ይዘው እንዲቀርቡ ማዘዛቸው ይታወሳል።
በአውሮፕላን ማረፊያዎች ውስጥ የተጀመረው የምርመራ አገልግሎት በርካታ መንገደኞችን ከእንግልት የሚታደግ ነው ተብሏል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ

