አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ተከስቶ የነበረውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ውይይቶች እየተካሄደ ነው፡፡
በውይይቱ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰንን ጨምሮ የፌደራል የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ከግልገል በለስ ከተማ እና ከማንዱራ ወረዳ ሁሉም ቀበሌዎች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች ተገኝተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በመተከል ዞን ተከስቶ የነበረውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የህብረተሰቡን የአብሮነት ዕሴቶች የበለጠ የማጠናከር ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን በውይይቱ ላይ ተናግረዋል፡፡
በቀጠናው በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለውን የሰዎች ሞት እና ንብረት መውደም በዘላቂነት መፍትሄ ለማበጀት በዞኑ ስር ባሉ ሁሉም ወረዳዎች የህዝብ ለህዝብ ውይይቶችን በማካሄድ የማህበረሰቡን አብሮነት መልሶ ለመገንባት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ከመተከል ዞን ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

