አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል የሚገኙ አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች ተጨማሪ መማሪያ ክፍሎች እና የትምህርት ቁሳቁስ ካልተሟላላቸው ትምህርት ለመጀመር አስቸጋሪ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፋለ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉር ቆይታ፥ እስከ ጥቅምት 16 ቀን ሁሉም ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ለማድረግ ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በአንዳንድ ዞኖች የሚገኙ የትምህርት መምሪያ ሃላፊዎችም በትምህርት ቤቶች ውስጥ የውሃ እጥረት ፈተና ሆኖብናል ብለዋል።
ዶክተር ይልቃል ትምህርት ቤቶችን ዳግም ስራ ለማስጀመር እንቅስቃሴ ከተጀመረ የቆየ ቢሆንም አሁንም ድረስ ግን ያልተፈቱ ችግሮች እንዳሉ ጠቅሰዋል።
በክልሉ ከሚገኙ 9 ሺህ 700 ትምህርት ቤቶች መካከል ከኮሮና በፊት ማስተማር የሚችሉት 60 በመቶ እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከእነዚህ ውስጥ 25 በመቶዎች በሶስት ፈረቃ ማስተማር እንዲችሉ ዝግጅት መደረጉን ነው ያነሱት። ሌሎቹ 15 በመቶዎች አብዛኛዎቹ ሁለተኛ እና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች ሲሆኑ በሶስት ፈረቃ ማስተማር አይችሉም ብለዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን እርካቤ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን 1 ሺህ 17 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና 48 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ የቧንቧ ውሃ እና ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ውሃ ያላቸው 261 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና 33 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብቻ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
አቶ መስፍን በተለይም ምስራቅ በለሳን መሰል የተከዜ ተፋሰስ አካባቢዎች አሳሳቢ የውሃ ችግር ያለባቸው ትምህርት ቤቶች መሆናቸውንም ነው የጠቀሱት።
በቀጣይ እንደመፍትሔ መንገድ እስካለባቸው አካባቢዎች ድረስ በቦቴ በመጫን እንዲሁም በህብረተሰቡ ጉልበት በመጠቀም በጀሪካን ወደ ትምህርት ቤቶች ለማዳረስ መታሰቡንም አውስተዋል።
ዶክተር ይልቃል ችግሮችን ለመቅረፍ ከአማራ ዓቀፍ ልማት ማህበር (አልማ) ጋር በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሰው አሁን ላይ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ መደረግ ይኖርበታል ነው ያሉት።
ለዚህም በትምህርት ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ባለድርሻ አካላት ፈጣን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በስላባት ማናዬ

