Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ወቅታዊ ስጋቶችን በመከላከል ሃገር የማሻገር ትውልዳዊ ተልዕኮን መወጣት ይገባል – ዶ/ር አብረሃም በላይ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 11 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለአፍራሽ ፕሮፖጋንዳ ጆሮ ባለመስጠትና የተጋረጡ ወቅታዊ ስጋቶችን በመከላከል፣ ሰላምና መረጋጋትን ማስጠበቅና በልማት ሃገር የማሻገር ትውልዳዊ ተልዕኮን መወጣት እንደሚገባ የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ዶክተር አብረሃም በላይ ጥሪ አቀረቡ።
 
ዶክተር አብረሃም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለኢዜአ በላኩት መግለጫ ÷ መላው ህዝብ የዜጎችን አብሮ የመኖር እሴትን በመናድ ህዝብን ከህዝብ መነጠል ዋነኛ ስራቸው አድርገው ከሚንቀሳቀሱ ቡድኖች በመጠበቅና ሴራቸውን በማክሸፍ ለአብሮነቱ ዘብ ሊቆም ይገባል ብለዋል።
 
በሃገሪቱ በተደረገው ለውጥ በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች የሚታይና አሳታፊ ለውጥ መምጣቱንም ተናግረዋል።
 
ይህ ያልተዋጠላቸውና አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለማፈራረስ የሚተጉ ኃይሎች አሁንም ህዝቡን እያዋከቡና እያጋጩ መሆኑንም አንስተዋል።
 
አፍራሽ ቡድኑ በህዝቦች መካከል መጠራጠርና አለመተማመን ማንገስን እንደ ዋና የህልውናና በስልጣን የመቀጠል መርህ አድርጎ መውሰዱንም ጠቅሰዋል።
 
ለረጅም ዘመን ህብረ ብሔራዊ አንድነቱን ጠብቆ የኖረውን፣ ሐይማኖት፣ ዘርና ጎሳ ሳይለይ ዳር እስከዳር ተዋልዶ ተሳስቦና ተከባብሮ የኖረውን ህዝብ፣ ሰውሮ ባስቀመጠው የልዩነት ካርድ በመጠቀም ታሪክ ይቅር የማይለውን ደባ ያለ ሀፍረት ቀጥሏል ብለዋል።
 
በተለይም በስሙ እየተነገደበት ያለው የትግራይ ህዝብ ከወንድም ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በመተባበር ነጻነቱን በብልሃት ማወጅ ይጠበቅበታልም ነው ያሉት።
 
መላው የትግራይ ህዝብ በውጭ የሚገኙ የክልሉ ተወላጆችና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በጋራ በመሆንና በጥበብና በማስተዋል ነገን በጋራ መገንባት እንደሚያስፈልጋቸውም አጽንኦት ሰጥተዋል።
 
ጊዜው እጅግ ማስተዋልና የላቀ የሃገር ባላደራነት የሚጠይቅ ነው ያሉት ዶክተር አብረሃም÷ ወቅቱ አፍራሽ ሃይሎችን በተባበረ ክንድ የመደርመስ ስራ የሚሰራበት መሆኑንም አውስተዋል።
 
መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከትግራይ ህዝቦች ጋር በመሰለፍ በተለያየ ጊዜ መንግስት የሚወስዳቸውን የተጠኑ ፖለቲካዊ እርምጃዎች በመደገፍና ለአፍራሽ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻዎች ጆሮ ባለመስጠት ከፊት የተጋረጡ የወቅቱ ስጋቶችን መከላከል ይገባዋልም ነው ያሉት ዶክተር አብረሃም።
 
 
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
Exit mobile version