Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሀረሪ ክልል በድንገተኛ አደጋዎች ሊያልፍ የሚችለውን የሰው ህይወት ለመቀነስ ቅንጅታዊ አሰራር ሊተገበር እንደሚገባ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በድንገተኛ አደጋዎች ሊያልፍ የሚችለውን የሰው ህይወት ለመቀነስ ቅንጅታዊ አሰራር ሊተገበር እንደሚገባ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ አስታወቁ።

የክልሉ የድንገተኛና ፅኑ ህሙማን እንክብካቤ ማሻሻያ ፕሮግራም ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተከናውኗል።

በዚህ ወቅት የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ከጥራት ጋር ለማረጋገጥ ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን በየጊዜው በሚያጋጥሙ ድንገተኛ አደጋዎች ሳቢያ የሚደርሰውን የሰው ህይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት ለማስቀረት ቅንጅታዊ አሰራርን መተግበር ወሳኝ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አመላክተዋል።

የድንገተኛና የፅኑ ህሙማን እንክብካቤ እጅግ አስፈላጊ ቢሆንም ተገቢው ትኩረት እንዳልተሰጠው የገለፁት አቶ ኦርዲን የእንክባካቤ ማሻሻያ ፕሮግራም በሀረሪ ከተማ መጀመሩ ለምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

በምስራቅ ኢትዮጵያ ከመልክአ ምድር አቀማመጡ ጋር ተያይዞ ይደርሱ ለነበሩ ድንገተኛ አደጋዎች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ባለመቻሉ በቀላሉ ሊድኑ በሚችሉ አደጋዎች የሠዎች ህይወት ያልፍ እንደነበር ተገልጿል።

ይህን ችግር ለመቅረፍ የተጀመረው የድንገተኛና የፅኑ ህሙማን እንክብካቤ ማሻሻያ ፕሮግራም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለውም ነው የተገለጸው።

ይፋ የተደረገው ፕሮግራም ዋነኛ ዓላማ በድንገተኛ አደጋ ወቅት አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ባለመቻል የሚያጋጥምን ሞትና የአካል ጉዳት ለማስቀረት እንዲሁም በፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገኙ ታካሚዎችን የእንክብካቤ ሁኔታ ለማሻሻል እንደሚያስችል የተገለፀ ሲሆን ከሌሎች ጋር በትብብርና በቅንጅት እንደሚሰራም ተመላክቷል።

ፕሮግራሙ ለጊዜው በአምስት አምቡላንሶች የሚጀመር ሲሆን በቀጣይ ራሱን ችሎ በሚገነባ ማዕከል አማካኝነት ለድንገተኛ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ የመስጠቱ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል።

በተሾመ ኃይሉ

Exit mobile version