አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 12 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በብሔር አስተዳደር፣ በብዝኅነት አያያዝ እና በሃይማኖቶች የጋራ እሴት ላይ ያተኮረ ኮንፈረንስ በጅማ እየተካሄደ ነው።
ኮንፈረንሱ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑ ተመላክቷል።
በኮንፈረንሱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ÷ የኮንፈረንሱ አጀንዳዎች ከምን ጊዜውም በላይ በአሁኑ ወቅት ሊሰራባቸው የሚያስፈልጉ አንኳር ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።
በመሆኑም በኮንፈረንሱ የሚገኘውን ግብዓት ተሣታፊዎች እስከ ታችኛው መዋቅር አውርደው እንዲሰሩበት ጥሪ አቅርበዋል።
ከዚህ ቀደም በጎማና በአጋሮ የተከናወኑ አበረታች የሠላም እሴት ግንባታ ሥራዎችም በሁሉም ወረዳዎች ይስፋፉ ዘንድ ተሣታፊዎች ጠንክረው በጋራ እንዲሰሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በኮንፈረንሱ ላይ ከጅማ ከተማ፣ ከጅማ ዞን፣ ከአጋሮ፣ ከጎማ፣ ከሰኮሩ፣ ከኦሙናዳ እና ከተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ ወጣቶች እና ሴቶች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት መሣተፋቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

