አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በደቡብ ክልል በጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች 4 ሚሊየን ብር የሚገመት የገንዘብ እና የአይነት ድጋፍ አበረከተ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የገንዘብ እና 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የአይነት በጠቅላላው የ4 ሚሊየን ብር ድጋፍ ለክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ አስረክበዋል፡፡
በርክክቡ ወቅት ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት ለወገኖች አብሮነነትን፣ ፍቅርን እና አጋርነትን መግለጽ መቻል ሁልጊዜ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ነው ብለዋል፡፡
እርስ በእርስ መደጋገፍ ካልተቻለ ከሌላ ከየትም ሊመጣ አይችልም ያሉት ምክትል ከንቲባዋ ወደፊትም በክልሉ ካሉ ህዝቦች ጋር ከባህል ትስስር ጀምሮ በእህትማማችነት እና ወንድማማችነት የተጀመረው ትስስር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ በበኩላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላደረገው ድጋፍ በደቡብ ህዝቦች ስም ምስጋና ማቅረባቸውን ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአራት ክልሎች በክረምቱ በጎርፍ አደጋ ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለማቋቋም የ29 ሚሊየን ብር የሚገመት የገንዘብ እና የአይነት ድጋፍ ለማድረግ በወሰነው መሰረት ባለፈው ለአፋር ክልል ወጣቶችን እና በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦችን በማስተባበር 10 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የቁሳቁስ እና የ2 ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

