Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ብሄራዊ ፓርኮችን ከእሳት አደጋ የሚከላከል የእሳት አጥፊ ብርጌድ ተቋቋመ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 14 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በብሄራዊ ፓርኮች ላይ የሚከሰት የእሳት አደጋን የሚቆጣጠር የእሳት አጥፊ ብርጌድ ማቋቋሙን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በብሄራዊ ፓርኮች ላይ የሚከሰትን የእሳት አደጋዎች በአፋጣኝ ለመቆጣጠር ፓርኮቹን ከሚያጎራብቱ የህብረተሰብ ክፍሎች የመለመላቸውን የእሳት አጥፊ ብርጌዶች አሰልጥኖ ወደ ስራ ማስገባቱን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራ ተናግረዋል፡፡

የእሳት አጥፊ ብርጌዶቹ በፓርኮች ላይ የእሳት አደጋ እንዳይከሰት ክትትል ከማደረጋቸውም በተጨማሪ ህብረተሰቡ በንቃት አካባቢውን እንዲቆጣጠር የማንቃት ስራ እንደሚሰሩም አክለዋል፡፡

በሌላ በኩል በፓርኮቹ ላይ የሚታዩትን ህገ-ወጥ የአደን ስራዎችን ለመቆጣጠር ግንዛቤ እየተሰጠ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

ህገወጥ አደንና የእንስሳት ዝውውርን ለመቅረፍ ከሚሰጠው ግንዛቤ ባለፈ በተግባሩ የተሰማሩ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን አቶ ኩመራ አስረድተዋል፡፡

ባለስልጣኑ በዱር እንስሳት ላይ የሚደርስ ጉዳትን ለመቀነስ ከሚሰራው ስራ ባለፈ የቱሪስት መዳረሻ መሰረተ ልማት አቅርቦትን ለማሻሻል መስራቱን ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version