አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ኢንጅነር ታከለ ኡማ ከአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ጋር በመሆን የፖታሽ፣ ጨውና ብሮሚን ምርቶች ላይ እየተከናወኑ ያሉ የማዕድን ልማቶችን እየጎበኙ ነው።
ሚኒስትሩ አፍዴራ አካባቢ “ታናራሙ ኬሚካልስ” በተባለ የቻይና ኩባንያ በ57 ሚሊየን ዶላር ወጪ እየተገነባ የሚገኘው የብሮሚን ፋብሪካን ጎብኝተዋል፡፡
በቅርቡ ተጠናቆ ወደ ስራ እንደሚገባ የሚጠበቀው ይህ ፋብሪካ “ሀይድሮጅን ብሮማይድ አሲድ” አዘጋጅቶ ለውጪ ገበያ የሚያቀርብ ነው ተብሏል።
ፋብሪካው በዓመት 40 ሺህ ቶን የማምረት ዕቅድ ያለው ሲሆን ምርቱን ለውጪ ገበያ በማቅረብ በዓመት 12 ሚሊየን ዶላር የማግኘት እቅድ መያዙ ነው የተገለጸው።
የፋብሪካው ኃላፊዎች ለግንባታ የሚያስፈልጓቸው ግብዓቶች ሀገር ውስጥ ከገቡ በኋላ የመዘግየት ችግር እያጋጠማቸው መሆኑና ችግሮች እንዲፈቱላቸው ለሚኒስትሩ ጠይቀዋል፡፡
ፋብሪካው የገጠመውን የግብዓት አቅርቦት መጓተት በተመለከተ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር እንዲፈታላቸው እንደሚያደርጉና ኃላፊዎቹም ፋብሪካው በፍጥነት ወደ ምርት እንዲገባ ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
በተጨማሪም ሚኒስትሩ ከአቶ አወል አርባ ጋር በመሆን የአፍዴራ የጨው ማውጫን ጎብኝተዋል።
ከጨው ማምረት ሂደቱ ጋር የፍትሀዊነት ጥያቄዎች የሚነሱ ሲሆን እነዚህ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሰጣቸው ገልፀዋል።
ጨው የማውጣት የመጀመሪያዎቹ ሂደቶች በሰው ሀይል ሊሰሩ የሚችሉ በመሆናቸው ለአካባቢው ማህበረሰብ ክፍት መሆን እንዳለባቸው ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም ፋብሪካዎች ከፍተኛ ፋይናንስ የሚጠይቀው እሴት የመጨመር ተግባር ላይ ብቻ እንዲሰማሩ እንደሚደረግም ገልጸዋል።
ይህ በፍጥነት ተግባር ላይ እንዲውልም ከክልሉ ጋር በጋራ እንደሚሰራ ኢንጅነር ታከለ ኡማ መናገራቸውን ከማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

