አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲፋጠን ዘርፈ ብዙ ድጋፍ በማድረግ የካይሮ ሰዎች የሚያደርጉትን የእጅ አዙር ጫና እስከ መጨረሻው መቀልበስ እንደሚገባ ምሁራን ገለፁ፡፡
የውሃ ጂኦ ፖለቲካ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ እና የምጣኔ ሀብት ጉዳዮች ምሁሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊው ፕሮፌሰር ተሾመ አበበ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ አድርገዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ለግብፅ ወግነው የሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን አስቆጥቷል።
ይህም ኢትዮጵያውያኑ በየሚኖሩባቸው የዓለም አራቱ ማዕዘን አፀፋ ምላሽ እንዲሰጡም አድርጓቸዋል።
በአሜሪካ ምስራቅ ኢሊኖስ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ጉዳዮች ተመራማሪው አንጋፋው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ምሁር ፕሮፌሰር ተሾመ አበበ የትራምፕ አስተያየትን በንቀት የተሞላ አድርገው ወስደውታል።
ይህ ደግሞ ለእርሳቸው እና መሰል ትውልደ ኢትዮጵያውያን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንዲያሰሙ አስገድዷቸዋል።
ፕሮፌሰር ተሾመ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከአሁን በፊትም ለአፍሪካውያን እና ለጥቁሮች ያላቸው አስተያየት የተዛባ መሆኑን ይገልጻሉ።
አሁንም በኢትዮጵያ ላይ የሰነዘሩት አስተያየት ከዚያ የተራዘመ ነው ያሉት ምሁራኑ የአፍሪካ ህብረት በፍጥነት መግለጫ አለማውጣቱ እንዳስገረማቸውም አንስተዋል።
በተቃራኒው የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ያወጣውን መግለጫ አድንቀዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ የትራምፕን አስተያየት ለበጎ ተፅእኖ መጠቀም አለብን ያሉ ሲሆን ትራምፕ ከመደበኛው የዲፕሎማሲ ተግባቦት አፈንግጠው የተናገሩት ነገር ቢኖር የካይሮ ሰዎችን የውስጥ ገመና ስለመሆኑም ያነሳሉ፡፡
ኢትዮጵያ የግድቡን ደህንነት ለማስጠበቅ እየወሰደች ያለውን እርምጃ ማጠናከር እንደሚገባትም ጠቁመዋል።
የግድቡ ግንባታ መፋጠን አለበት የሚሉት ምሁራኑ የትራምፕ አስተያየት የኢትዮጵያውያን አንድነት እንዲጠናከር ያደርጋልም ነው ያሉት።
ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ አፍሪካ ከእርዳታ ዲፕሎማሲ ልትወጣ እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡
ሰሞነኛው የትራምፕ ድጋፍ አታገኙም ማስፈራሪያም ግድቡን በማጠናቀቅ ልማትን በማፋጠን ሊቋጭ ይገባል ነው የሚሉት።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ተመራማሪው ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ ደግሞ ከውጭ የተቃጣውን የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ለመመከት ውስጥን መፈተሽ ያገባል ብለዋል።
በየጊዜው በተለያዩ አካባቢዎች በንፁሃን ላይ የሚፈፀሙ ግድያዎች መነሻ እና ግብ ተጣርቶ፤ ከጥቃቱ በስተጀርባ ያሉ አካላት ከእነማን ጋር እየሰሩ ነው የሚለውም
ሳይድበሰበስ ለህዝብ ይፋ መደረግ እንዳለበትም ምክረ ሀሳብ አስቀምጠዋል።
እነዚህን ሁነቶች በአጭር ጊዜ እልባት በመስጠት የግብፃውያንን የእጅ አዙር ጦርነት ለመመከት መዘጋጀት የግድ መሆኑንም ያስረዳሉ።
በስላባት ማናዬ

