አዲስ አበባ ፣ጥቅምት 22፣ 2013 ( ኤፍ.ቢ.ሲ)- ቱሪዘምና ሰላምየማይነጣጠሉ ጉዳዮች መሆናቸውን ተገንዝበን መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ቡዜና አብዱልቃድር አስታወቁ ።
የዓለም የቱሪዝም ቀን በኦሮሚያ ክልል ደረጃ በሻሸመኔ ከተማ እየተከበረ ነው ።
በበዓሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ሚኒስትር ዴአታዋ በወቅቱ እንደገለጹት በሀገራችን በሁሉም ክልሎች በርካታ የቱሪዝም ፀጋዎች አሉ÷ ይሁንና ፀጋዎቹን አልምተን ወደ አገልግሎት ማስገባት ላይ ብዙ ስራ ይቀረናል ብለዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ የተደረገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ቱሪዝምን ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ማድረጉን ተናግረዋል ።
በቱሪዝም የዜጎችን ህይወት ወደ ብልፅግና ለመውሰድ በሁሉም ክልሎች እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል ።
አያይዘውም የኮቨድ 19 ፕሮቶኮልን በመጠበቅ መስህቦችን ማልማትና የጎብኚዎችን ደህንነት መጠበቅ የሁሉም ሥራ ሊሆን ይገባል ብለዋል ።
ቱሪዝምና ሰላም የማይነጣጠሉ ጉዳዮች በመሆናቸው ኦሮሚያን ጨምሮ ሁሉም ክልሎች ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ዘርፉን ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።
የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኅላፊ አቶ ከበደ ደሲሳ በበኩላቸው ÷ የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ የመሰረተ ልማቶች ግንባታና መስህቦችን የማሳወቅ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል ።
የአሁኑ የኦሮሚያን እናስተዋውቅ ጉዞም በኮሮና ቫይረስ ክስተት የተጎዳውን የዘርፉን ኢኮኖሚ መልሶ እንዲያገግም ማስቻል ዓላማ ያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል ።
ኮሮና ቫይረስን እየተጠነቀቅን ሰላም የሰፈነባትን ኦሮሚያ በመጉበኘት ቱሪዝምን እናሳድግም ነው ያሉት ።
የምእራብ አርሲ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበራ ቡኖም ምእራብ አርሲ የ13 ወር ፀጋ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል ።
የብዙ ሐይቆችና ብሔራዊ ፓርኮች መገኛ የሆነው ዞኑ የሀገሪቱ የቱሪዝም የጀርባ አጥንት ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

