“የሀረሪ ክልል ህዝብና መንግስት የዜጎችን ደህንነትና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚወሰዱ እርምጃዎችን ለማሳካት በግንባር ቀደምትነት እንሰለፋለን”
መከላከያ ሠራዊታችን የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊነት ለማስከበር፣ ሰላምና ደህንነታቸውን ለመጠበቅ የገነቡት ጠንካራ ብሔራዊና ሀገራዊ ተቋም ለመሆኑ በተግባሩ ደጋግሞ አረጋግጧል።
ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መሠረት አድርጎ የተሰጠውን ተልዕኮ በላቀ ወታደራዊ ዲስፕሊንና ብቃት በመወጣት ከራሱ አገርና ህዝብ አልፎ በአህጉራዊና አለም አቀፋዊ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ታላቅ ከበሬታ፣ አመኔታና ይሁንታ ያተረፈ ተቋምና ሰራዊት እንደሆነም ይታወቃል።
ሰላምና ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ሌት ተቀን ዘብ በቆመበትና ከመቼውም ጊዜ በላይ አገራዊ አንድነትና ሰላም በሚያስፈልግበት በአሁኑ ወቅት ተስፋ የቆረጠው የህወሓት የጥፋት ቡድን ትግራይ በሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ካምፕ ላይ የፈጸመው አገር የማፍረስ ግልጽ ሙከራ በመላው የኢትዮጵያ ህዝብና በሉዓላዊነታችን ላይ የተፈጸመ አሳፋሪ ተግባር ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
በመሆኑም እንደ ቁማር ማስያዣ ሲጠቀምበት ከኖረው ሰላም፣ እኩልነትና አንድነት ወዳዱ የትግራይ ህዝብ መሃል የመሸገው የህወሓት የጥፋት ቡድንን ከነተላላኪዎቹ ለይቶ ለማጽዳት መንግስትና ሰራዊቱ የሚወስዱትን ማናቸውም አጸፋዊ ምላሽ ከመደገፍ ባለፈ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአንጸባራቂ ድል እንዲጠናቀቅ የሀረሪ ክልል መንግስትና ህዝብ ከሰራዊታችን ጎን በመሰለፍ የህይወት መስዋዕትነት ጭምር ለመክፈል ያለውን ዝግጁነትና ቁርጠኝነት ያረጋግጣል።
በዚህ አጋጣሚ መላው የክልላችን ህዝብ ከምንጊዜውም በላይ የአካባቢውን ሰላምና ጸጥታ በከፍተኛ ትኩረትና ንቃት ከመጠበቅ ባሻገር በመንግስትና በሚመለከታቸው አካላት የሚሰጡትን መግለጫዎች በትኩረት እንዲከታተል ጥሪ ያስተላልፋል።
የሀረሪ ህዝብ ክልላዊ መንግስት
ጥቅምት 25/2013
ሀረር

