Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ እያካሄደ ነው።

ምክር ቤቱ 5ኛ ዙር 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ጉባኤ ነው የሚያካሄደው፡፡

ምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤውን ሲጀምር በቅርቡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የተለያዩ ወረዳዎች፣ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ እንዲሁም በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ጉራፈርዳ ወረዳ በአማራ ህዝብ ላይ በተፈጸመው አሰቃቂ ጅምላ ጭፍጨፋ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች የህሊና ጸሎት አድርጓል፡፡

ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት አፈ ጉባኤ ወርቀሰሙ ማሞ በቅርብ በተለያዩ አካባቢዎች የደረሰውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ የህዝባችን ልብ የሰበረና የማንረሳው በመሆኑ የተሰማኝን ሀዘን እገልጻለሁ ብለዋል፡፡

አፈ ጉባኤዋ በንግግራቸው በሀገር ላይ ክህደት የፈጸመው ህወኃት ወደ ሥልጣን ለመመለስ የወሰደው አማራጭም ሀገርን የማተራመስ የለየለት የሽብር ተግባርና የሀገር ክህደት ወንጀል ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም በሀገር መከላከያ ሰራዊትና በክልሉ ህዝብ ላይ የጀመረውን ጥቃት መክተን እየሄድንበት ያለው የማጥቃት ድል ለሀገራችን ህዝቦች ዘላቂ ሰላምን የሚያመጣ እንዲሆን የህዝባችን ርብርብ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል በጉባኤው፡፡

ህወኃት ከምስረታው ጀምሮ በተሳሳተ መንገድ የአማራን ህዝብ ለሥልጣን ማራዘሚያው ፈርጆ ሲጠቀምበት እንደነበር ይታወቃል ያሉት አፈጉባኤዋ ይህንን ትርክት ከለውጡም በኋላ ተሻጋሪ ለማድረግ ተላላኪዎቹን በማሰለፍ አሰቃቂ ጉዳቶችን አድርሷል ነው ያሉት፡፡

የምክር ቤቱ አባላት እንደ ህዝብ እንደራሴነታቸው ህዝቡን በማንቃትና በማደራጀት ትግሉን በአሸናፊነት እንዲወጡ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የክልሉ የሰላምና የህዝብ ደኅንነት ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ለምክር ቤቱ አጭር ሪፖርት አቅርበው ውይይት እንደተካሄደበት ተጠቅሷል፡፡

በቀረበው ሪፖርት መሰረትም የህግና ፍትህ ቋሚ ኮሚቴ የውሳኔ ሀሳቦችን አቅርቧል፡፡

የምክር ቤቱ አባላትም ህወኃት የአማራ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት መሆኑን ያስመሰከረ ድርጅት በመሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ተባብሮ የጀመረውን ትግል በድል እንዲያጠናቅቅ በአንድነት መቆም እንደሚገባ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በሀገር ላይ ክህደት የፈጸመው ህወኃት ያለምንም ድርድር እስከ መጨረሻው በመፋለም የኢትዮጵያን ህዝብ ሰቆቃ ማስቆም ይገባልም ማለታቸውን ከአማራ ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

Exit mobile version