አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውጤታማነት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ በዓለም ባንክ ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ኦስማን ዳይን ከተማራውን ልዑክ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
ውይይታቸውም በዋናነት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በተግዳሮትነት እየተነሱ በሚገኙት የሀይል አቅርቦት ውስንነት፣ የሰራተኞች የመኖሪያ ቤት ችግር እና በፍሳሽ ማጣሪያ ግንባታ ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል።
እንዲሁም ኮርፖሬሽኑን በዓለም አቀፍ መድረክ ከማስተዋወቅ አንጻር የሚታዩ ውስንነቶችን እና ሌሎቸ ተያያዥ ጉዳዮችን አንስተው ምክክር አድርገዋል።
በውይይቱ ላይም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ፥ የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን በመቆም ላለፉት በርካታ ዓመታት ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍ መንግስት በታላቅ አክብሮት እንደሚመለከተው ጠቅሰዋል።
የዓለም ባንክ ድጋፍ በኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ዘርፍም ተጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የዓለም ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ኦስማን ዳይን በበኩላቸው፥ ችግሮችን በቅደም ተከተል በመለየት መፍትሄዎችን መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፤ በሂደቱም ተቋማቸው የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት በኮርፖሬሽኑ እየለሙ ከሚገኙ ፓርኮች መካከል ቦሌ ለሚ 2 እና ቂሊንጦ ፋርማሲዩቲካል የኢንዱስትሪ ፓርክ ሙሉ በሙሉ ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በመገንባት ላይ ናቸው።

