አዲስ አበባ፣ ህዳር 7፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኑሮዋቸውን በጎዳና ያደረጉ ከ6 ሺህ በላይ ዜጎችን ለማቋቋም እየሰራ መሆኑን ገለጸ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ተፈራ ሞላ በተለያዩ ምክንያቶች ኑሮዋቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎችን ማንሳት ተጀምሯል ነው ያሉት።
እስካሁንም 2 ሺህ የሚሆኑ በክፍለ ከተሞች በተዘጋጁ ማቆያ ጣቢያዎች መግባታቸውን አስረድተዋል።
ጎዳና ተዳዳሪዎቹን ለማቋቋም አግባብ ካላቸው አካላት የተወከሉ 11 አባላት ያሉት ዓቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩን ኃላፊው ተናግረዋል።
በማዕከላቱ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የጤና ባለሙያዎች የተመደቡ ሲሆን፣ የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ እንደተሟላም አስረድተዋል።
ጎዳና ተዳዳሪዎቹ በሃገሪቱ በሚካሄዱ የልማት ፕሮጀክቶች ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑንም አቶ ተፈራ ገልጸዋል።
በተጨማሪም በመንግሥታዊና መንግሥዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ሥራ ይፈለግላቸዋል ብለዋል።
ለዚህም በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት የስልጠና ማዕከላት ተዘጋጅተው ፍላጎታቸውን መሰረት ያደረገ ስልጠና በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ኃላፊው ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

