Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን የትግራይ ወጣቶች የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖራቸው ሲሰራ መቆየቱን በቁጥጥር ስር የዋሉ የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን የትግራይ ወጣቶችን ‘እኔ ከሌለሁ መኖር አትችሉም’ እያለ የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖራቸው ሲሰራ መቆየቱን በቁጥጥር ስር የዋሉ የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት ተናገሩ።

ከልጅነታቸው ጀምሮ የተሳሳተ አመለካከት ይዘው እንዲያድጉ ለማድረግ ለበርካታ ዓመታት “ህወሓት ከወደቀ መኖር ስለማትችሉ ለማንኛውም ትግል ተዘጋጁ” ሲል መኖሩንም ተናግረዋል።

ቡድኑ ለልዩ ኃይሉ አባላት በቂ ስንቅ ስለማያቀርብላቸው በከፋ ችግር ውስጥ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

“በትግል ሂደት ደግሞ ያለእናንተ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊያሸንፍ የሚችል ኃይል በፍፁም የለም፣ አይኖርምም” በማለት ሲሰብክ ኖሯል ብለዋል።

ነገር ግን ጦርነት በተግባር አስከፊ መሆኑን ጓደኞቻቸው ከጎናቸው ሲወድቁ መረዳታቸውንም ነው የገለጹት።

አመራሮች እነሱን ተዋጉ ብለው ካሰለፉ በኋላ የት እንዳሉ ሳይነግሯቸው እንደሚጠፉም ለኢዜአ ተናግረዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ በርካታ የትግራይ ልዩ ኃይል አባላት ለአገር መከላከያ ሠራዊት እጃቸውን በሠላም የመስጠት ፍላጎት ስላላቸው አጋጣሚውን ነው የሚጠብቁት ብለዋል።

በጽንፈኛው ቡድን ያሉ ሴረኞች ክልሉን ያለወጣት እያስቀሩት ነው በማለት በውስን ግለሰቦች ሴራ የትግራይ ወጣት መቀጠፍ እንደሌለበት አመልክተዋል።

በትግራይ ክልል ከህወሓት ትዕዛዝ የሚያፈገፍግ ወጣት ወይም ነዋሪ ካጋጠመ የሚወሰድበት እርምጃ ከባድ እንደሆነም ተናግረዋል።

እጃቸውን ለአገር መከላከያ ሠራዊት ከሰጡ በኋላ ምንም አይነት ችግር እንዳልደረሰባቸውና ሠራዊቱ እንክብካቤ እያደረገላቸው እንደሆነም ገልጸዋል።

የትግራይ ወጣት ላልተገባ ዓላማ ሕይወቱን መስዋዕት እያደረገ መሆኑን ተገንዝቦ በሠላማዊ መንገድ እጁን ለመከላከያ ሠራዊት እንዲሰጥም ጥሪ አቅርበዋል።

የህወሓት የጥፋት ቡድን ታዳጊ የትግራይ ወጣቶችን ከቤተሰቦቻቸው በመነጠል በሚያደርገው አፈናና የጥፋት ተልዕኮ በርካታ ወላጆች ሃዘን እንደገባቸውም የልዩ ኃይል አባላቱ አስረድተዋል።

የትግራይ ወጣቶች በህወሓት የተሰበኩትን የተሳሳተ ትርክትና የስነ ልቦና ጭንቀት ለማስተካከል መንግስት አስፈላጊውን እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

መንግስት የጀመረውን ሕግ የማስከበር እርምጃ በማጠናከር ሕዝቡን በፍጥነት ነፃ እንዲያወጣና ወጣቶችንም ከእልቂት እንዲታደግ ጥሪ አቅርበዋል።

Exit mobile version