አዲስ አበባ ፣ ህዳር 10 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፖሊስ የደንብ ልብስ በመልበስ ወርቅ የሰረቁ ተጠርጣሪዎች ከእነኤግዚቢቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የግል ተበዳይ አቶ አቤል አሰፋ ህዳር 4 ቀን 2013 ዓ.ም ከጠዋቱ 12 ሰዓት ገደማ ፖሊሶች ነን ያሉ ግለሰቦች በአራዳ ክፍለከተማ ወረዳ 6 ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው መጥተው በር እንዲከፍቱላቸው ሲጠይቋቸው ማንነታችሁን ሳላረጋግጥ እና ለቤተሰቦቼ ሳላሳውቅ አልከፍትም ማለታቸውንና ፖሊስ ነን ያሉት ግለሰቦች ተጨማሪ ሃይል ያስፈልገናል እያሉ እየተነጋገሩ ወደመጡበት እንደተመለሱ ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ የግል ተበዳይ አቶ አቤል ቀን ወደ ስራ ከሄዱ በኋላ ተጠርጣሪዎቹ ከቀኑ 9 ሰዓት ሲሆን የፖሊስ የደንብ ልብስ ለብሰው እና ሽጉጥ ታጥቀው ተመልሰው በመምጣት ” አቶ አቤል ወንጀል ሰርተው ስለታሰሩ እኛ ቤታቸውን ልንበረብር ነው የመጣነው ” ብለው ለጎረቤት ከተናገሩ በኋላ የተቆለፈውን በር ሰብረው በመግባት በካዝና ውስጥ ለንግድ አገልግሎት የተቀመጡ አንድ ሚሊየን ሶስት መቶ ሺህ ብር ግምት ያላቸውን የወርቅ ጌጣጌጦችን ሰርቀው የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 4-20411 አ.አ በሆነ ፒካፕ ተሽከርካሪ ጭነው መውሰዳቸውን የግል ተበዳይ ገልፀዋል፡፡
በአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የጃን ሜዳ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ለውጥአየሁ ከበደ÷ የወንጀሉ መፈፀም ሪፖርት የደረሰው ጣቢያው የምርመራ እና የክትትል ቡድን በማቋቋም እና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የክትትል ክፍል ጋር በመቀናጀት ውጤታማ ስራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡
በዚህም የፈፃሚዎቹን ማንነት ለማወቅ በተደረገው ክትትል ካዝናውን ጭኖ የተሰወረውን ተሽከርካሪ፣ በወንጀሉ ተሳትፈዋል የተባሉ 5 ተጠርጣሪዎችን፣ ለወንጀል ተግባር ሲጠቀሙባቸው የነበሩ የፖሊስ የደንብ አልባሳት፣ ሽጉጥ፣ ካቴና እና ስለቶችን በቁጥጥር ስር ማዋል እንደተቻለ ተናግረዋል።
የፖሊስ የደንብ አልባሳቱንም ከየት አምጥተው እንደለበሱ የማጣራት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ዋና ኢንስፔክተር ለውጥአየሁ ከበደ ተናግረዋል፡፡
የተሰረቁት ወርቆች በ600 ሺህ ብር ለሌላ ግለሰብ ተሸጠው እንደነበር ያስታወሱት ምክትል ኢንስፔክተር ሄኖክ የተሸጡት ወርቆች መርካቶ አካባቢ እንደተገኙ እና ገዢውም በቁጥጥር ስር እንደዋለ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ፖሊስ ቀንና ሌሊት ደክሞ በመስራትና ተጠርጣሪዎቹን አውቆ በመያዝ ያከናወነው ተግባር እንዳስደሰታቸው የግል ተበዳይ አቶ አቤል አሰፋ ተናግረዋል፡፡
ምርመራውን ለማስፋት በተደራጀ መንገድ እየተሰራ ነው ያሉት ዋና ኢንስፔክተር ለውጥአየሁ ከበደ ፖሊስ ሳይሆኑ የፖሊስ የደንብ ልብስ ለብሰው ወንጀል የሚፈፅሙ እና የከተማዋን ፀጥታ ለማደፍረስ የሚንቀሣቀሱ ግለሰቦች በመኖራቸው ህብረተሰቡ መታወቂያ በመጠየቅም ሆነ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ስልክ በመደወል ህጋዊነታቸውን ሊያረጋግጥ እና አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙም ለሚመለከተው አካል ሊያሳውቅ ይገባል ማለታቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

