Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወያየ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በዛሬው እለት ውይይት አካሂዷል።

በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሩያ ትኩረቱን ያደረገው ውይይት ላይም በትግራይ ክልል የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋን ጨምሮ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ተገኝተዋል።

በመድረኩም በክልሉ ሰላም ለማምጣት በሚደረጉ ጥረቶች ዙሪያ ምክክር ተደርጓል።

እንዲሁም በጊዜያዊ አስተዳደሩ በቀጣይ ሊሰሩ በታሰቡ ሰላም የማስፈን እና ሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ምን መምሰል አለበት የሚለው ላይም ሀሳብ ተነስቶ ውይይት ተደርጎበታል።

በትግራይ ክልል የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ፥ በክልሉ ሊሠሩ የታሰቡ ሥራዎች ዙሪያ ለተሳታፊዎቹ ገለፃ አድርገዋል።

በዚህም ባለ ስድስት ነጥብ ረቂቅ ቻርተር ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው፥ ከእነዚህም ውስጥ የአስተዳደር መዋቅር ማስተካከል እና የክልሉ ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ ማድረግ በቻርተሩ መዘርዘራቸውንም ነው የተናገሩት።

በተጨማሪም በትግራይ ክልል ሰላምንና ደህንነትን ማረጋገጥ፣ የህግ የበላይነትን እና ፍትህን ማስጠበቅ፣ በክልሉ ተቋረጠውን ማኅበራዊ አገልግሎት ማስቀጠል እና ፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራዊ ምርጫ በነፃነት እንዲወዳደሩ ማስቻልም በቻርተሩ ተዘርዝረዋል።

Exit mobile version