Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኮሚሽኑ የካርጎ ትራኪንግ አገልግሎት ለማሻሻል ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጉምሩክ ኮሚሽን የካርጎ ትራኪንግ አገልግሎትን ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ ለመደገፍ ከትሬድ ማርክ ኢስት አፍሪካ ኩባንያ ጋር ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ስምምነቱን የጉምሩክ ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ እና የትሬድ ማርክ ኢስት አፍሪካ ኩባንያ ተወካይ አቶ ታደሰ ይማሙ ተፈራርመውታል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ እንደተናገሩት÷ ኮሚሽኑ በአዲስ መልክ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የጉምሩክ አገልግሎቱን ምቹ፣ ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

የራሱን አቅም ከማሳደግ ጎን ለጎን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በተለይም በድንበሮች አካባቢ ያለውን የገቢና ወጪ ዕቃዎችን ፍሰት ጤናማ፣ ቀልጣፋና ግልፅ ለማድረግ የካርጎ ትራኪንግ ቴክኖሎጂ ወሳኝ በመሆኑ ከኩባንያው ጋር በዚህ ረገድ በትብብር ለመስራት ዝግጅት መጠናቀቁንም ጠቁመዋል፡፡

ቴክኖሎጂው በጉምሩክ ክልል ውስጥ የሚጓጓዙ ዕቃዎች ያሉበትን ሁኔታ፣ የደረሱበትን ቦታና አሁናዊ መረጃ በግልፅ ከማሳየቱም በላይ በህጋዊ ዕቃዎች ውስጥ የሚገቡ ህገወጥ ዕቃዎችን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል፡፡

የትሬድ ማርክ ኢስት አፍሪካ ኩባንያ ተወካይ አቶ ታደሰ ይማሙ በበኩላቸው ÷ ድርጅታቸው በተለይም በምስራቅ አፍሪካ የጉምሩክ አገልግሎትን ለማቀላጠፍ በሚሰሩ ስራዎች በመሳተፍ ከፍተኛ ልምድ ያለው ነው ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በ18 ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ጠቅሰው ጥናቶች ተደርገው የማሽን ተከላ ከማድረግ ባሻገር ለሰራተኞች የተለያዩ ስልጠናዎች እንደሚሰጡ መግለፃቸውን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version