አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሱዳን የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ከሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኡመር ጋማር አልዲን ኢስማኤል ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸው ወቅትም አምባሳደር ይበልጣል በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ገለፃ ማድረጋቸውን በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።
በዚህም አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ የፌደራል መንግስት በህወሓት የጥፋት ቡድን ላይ እያካሄደ ያለውን ህግ የማስከበር ዘመቻ ከመንስኤው ጀምሮ አሁን ያለበት ደረጃ በተመለከተ ለተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገለፃ አድርገዋል።
አምባሳደር ይበልጣል በገለፃቸው፥ ህግ የማስከበር ዘመቻው አሁን ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን፣ ተጨማሪ ጉዳት ለመቀነስ የህወሓት የጥፋት ቡድን በሰላማዊ መንገድ እጅ እንዲሰጥ መጠየቁን ገልፀዋል።
በተጨማሪም የህወሓት የጥፋት ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት የመፈፀመ፣ የዘር ጭፍጨፋ ያደረገ፣ በህዝቦች መካከል የእርስ በእርስ ግጭት እንዲፈጠር በገንዘብ እና በሎጅስቲክስ ድጋፍ በማድረግ በርካታ ወንጀል ከፈጸመ የጥፋት ቡድን ጋር ድርድር ማድረግ እንደማይቻልም አብራርተዋል።
በቀጣይ ጥቂት ጊዜያት ውስጥ ቡድኑ ለፍርድ እንደሚቀርብም ነው በገለጻቸው ያነሱት፡፡
የሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኡመር ጋማር አልዲን ኢስማኤል በበኩላቸው፥ ጉዳዩን በቅርበት እንደሚከታተሉት፣ የተደረገላቸው ገለፃ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት እንደረዳቸው አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያና ሱዳን ወንድም እና እህት የሆኑ ሀገሮች በመሆናቸው እንደ ቤተሰብ የኢትዮጵያ ጉዳት እንደሚሰማቸው እንዲሁም በስደተኞች ጉዳይ ተባብረው እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

