አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ መንግስት ከህወሓት የጥፋት ቡድን ጋር ለውይይት አይቀመጥም ሲሉ ገለፁ፡፡
አምባሳደሩ ከፍራንስ 24 የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ቡድኑ በንፁሀን ዜጎች ላይ ጥቃት መፈፀሙን አንስተዋል፡፡
ጁንታው ንፁሀን ዜጎችን ከማጥቃቱ በተጨማሪ፣ የሀገር ደጀን በሆነው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ክህደት መፈፀሙን ተናግረዋል፡፡
ዜጎች ላይ አሰቃቂ ግድያ መፈፀም በኢትዮጵያ ህግ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ህግም ያስጠይቃል ነው ያሉት፡፡
የኢፌዴሪ መንግስትም ከዚህ ወንጀለኛ ቡድን ጋር ለድርድር የሚቀመጥበት ምንም ምክንያት የለውም ብለዋል፡፡
አምባሳደር ሄኖክ ቡድኑ ሲቀርብለት የነበረውን የሰላም ጥሪ ወደ ጎን በመተው የኃይል አማራጭ በመከተሉና ጥፋት እየፈፀመ በመሆኑ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
የህወሓት ጁንታ ቀድሞ የሰላም በሮችን በመዝጋቱና ከጥፋቱ ተምሮ ባለመፀፀቱ መንግስት ሀገር የማስቀጠል ግዴታ ስላለበት ህግን ያስከብራል ሲሉም ገልፀዋል፡፡

