Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሶዶ -ኦሞ ወንዝ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ግንባታ ስራ 76 በመቶ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 76 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የሶዶ -ኦሞ ወንዝ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ግንባታ ስራ 76 በመቶ ተጠናቀቀ፡፡
ፕሮጀክቱ ከሶዶ ከተማ 7 ኪሎ ሜትር ላይ በመነሳት ኦሞ ወንዝ ላይ የሚያበቃ ሲሆን ግንባታው በሚጠናቀቅበት ወቅት ወደ ግልገል ጊቤ 3 የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ ፍጥነት ለመድረስ ያስችላል ተብሏል።
እንዲሁም ከሶዶ ተነስቶ የኦሞ ወንዝ ለመድርስ ከ2 ሰዓት በላይ ይፈጅ የነበረውን በተሽከርካሪ የሚደረግን ጉዞ በአማካኝ በግማሽ ይቀንሰዋል ነው የተባለው።
የመንገድ ፕሮጀክቱ የጎን ስፋት በወረዳ 21 ነጥብ 5 ሜትር በቀበሌ 12 ሜትር እንዲሁም በገጠር የመንገድ ትከሻን ጨምሮ 1ዐ ሜትር ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ እየተገነባ ነው።
ሁናን ሁንዳ ሮድ ኤንድ ብሪጅ ኮርፖሬሽን የተባለው የቻይና ኩባንያ ግንባታውን እያከናወነው ሲሆን የማማከርና የቁጥጥር ሥራውን ደግሞ የተባበሩት የምህንድስና አማካሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እያካሄደው ይገኛል።
1 ቢሊየን 328 ሚሊየን 412 ሺህ ብር በጀት የተያዘለት የዚህ የመንገድ ፕሮጀክት ወጪ በኢትዮጵያ መንግስት እንደሚሸፈን ታውቋል፡፡
በተጨማሪም የዚሁ መንገድ ቀጣይ ክፍል የሆነው የሶዶ- ተርጫ በግንባታ ሂደት ላይ ሲሆን በሚጠናቀቅበት ጊዜ የጨበራ ጩርጩራን ጥብቅ ደን እንዲሁም በገበታ ለሃገር ድጋፍ የሚሰራውን የኮይሻ ፕሮጀክት ጋር በማስተሳሰር ለሀገሪቱ የቱሪስት መስህብ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል መባሉን ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
Exit mobile version