Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአዲስ አበባ የተለያዩ ጥቃቶችን ለመፈፀም እና የፀጥታ መደፍረስ እንዲከሰት አቅደው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከ700 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል – ፖሊስ ኮሚሽን

አዲስ አበባ፣ ህዳር 14፣ 2013 (ኤፍቢሲ) ከህወሃት ቡድን ተልዕኮ ተቀብለው በአዲስ አበባ የተለያዩ ጥቃቶችን ለመፈፀም እና የፀጥታ መደፍረስ እንዲከሰት አቅደው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከ700 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በሰሜን ዕዝ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ሀገሩን በካደው የህወሃት ቡድን የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት እየወሰደ ባለው ህግን የማስከበር እና የህልውና ዘመቻ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የታሰቡ የጥፋት ሴራዎች በህብረተሰቡ እና በፀጥታ አካላት ትብብር መምከናቸውን ነው ኮሚሽኑ የገለጸው፡፡

ቡድኑ ላለፉት 27 ዓመታት የዘረጋውን የግንኙነት መረብ ተጠቅሞ በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ሊፈፅም ያሰበው የሽብር ጥቃት እንዳይሳካ ከጥቅምት 25 ቀን ጀምሮ በተደረገ ጠንካራ የክትትል እና የቁጥጥር ስራ ከከሃዲው የህወሃት ጁንታ ተልዕኮ ተቀብለው የተለያዩ ጥቃቶችን ለመፈፀም እና የፀጥታ መደፍረስ እንዲከሰት አቅደው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 796 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ኮሚስኑ ጠቅሷል፡፡

እንዲሁም በርካታ የጦር መሳሪዎች እና ሌሎች ቁሳቁሶች በፍርድ ቤት የመበርበሪያ እና የመያዣ ትዕዛዝ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የልዩ ልዩ ህገ- ወጥ ዝውውር ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክተር ኮማንደር ግርማ ተሰማ አስታውቀዋል፡፡

በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚፈፀሙ ጥቃቶች እና የሚከሰቱ ግጭቶች በህወሃት ፊትአውራሪነት እና ድጋፊ ሰጪነት የሚፈፀሙ ስለመሆናቸው የሚያረጋግጡ እና ሃይማኖትን ከሃይማኖት፣ ብሄርን ከብሄር ለማጋጨት የተዘጋጁ ሰነዶች በብርበራ ወቅት መገኘታቸውን ኮማንደር ግርማ አስረድተዋል፡፡

ኮማንደር ግርማ እንደገለጹት የጁንታውን ቡድን ተልዕኮ የፀጥታ አካላትን የደንብ ልብስ በመልበስ ጭምር በአዲስ አበባም ለማስፈፀም ሲንቀሳቀሱ እና ዝግጅት ሲያደርጉ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ያስታወሱት፡፡

በተለያዩ ግለሰቦች መኖሪያ ቤት እና በልዩ ልዩ ተቋማት ውስጥ በተደረገ ፍተሻ 202 የተለያዩ የፀጥታ አካላት የደንብ አልባሳት ተይዘዋል ነው ያሉት፡፡

የደንብ አልባሳቶቹ በሃይማኖት አባቶች መኖሪያ ቤቶች ጭምር መገኘታቸውን የጠቀሱት ኮማንደር ግርማ ይህ ደግሞ ህገወጡ እና ከሃዲው የህወሃት ቡድን በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ሳይቀር ሰርጎ በመግባት ግጭት ለመቀስቀስ እየተንቀሳቀሰ አንደሚገኝ የሚያሳይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

እስካሁን ለተገኘው ውጤት የህብረተሰቡ ተሳትፎ የጎላ ሚና እንደነበረው ያስታወሱት ኮማንደር ግርማ ተሰማ አዲስ አበባ ላይ ጀምረን አዲስ አበባ ላይ እንጨርሰዋለን በሚል ከንቱ ምኞት ላይ ታች ሲሉ ህልማቸው የመከነባቸው የጥፋት ቡድኖች ምንም ዓይነት ቀዳዳ እንዳይኖራቸው እና በተለያዩ ተቋማት እና አካባቢዎች ተሰግስገው የሚገኙ ሌሎች የጥፋት መልዕክተኞችን በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

 

 

Exit mobile version