Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የዲማ – ራድ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 15፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያን ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚያስተሳስረው የዲማ – ራድ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አሰታወቀ።
የመንገድ ግንባታው 60 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ይህ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ መጠናቀቁ አማራጭ የገቢ ወጪ ንግድን ለማሳለጥ ከፍተኛ ተቀሜታን ያበረክታል ተብሏል።
እንዲሁም ትራንስፖርት ትስስርን ከማቀለጠፉም በላይ ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያላትን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ የማህበራዊ እና የኢኮኖሚ እና የንግድ ልውውጥን የተሳለጠ ከማድረግ አኳያ የመንገዱ ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል።
የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ ቡናን ጨምሮ የፍራፍሬ ፣ማር እና ቅመማ ቅመም ምርት ውጤቶችን ከምዕራቡ የአገሪቷ ክፍል ወደ ውጪ በመላክ ረገድ ሚናው የጎላ ሲሆን፥ በአካባቢው ያሉትን አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ታውቋል።
ፕሮጀክቱን በኢትዮጵያ መንግስት በተመደበ 856 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባ ሲሆን፥ በየኢትዮጵያ ኮንስተራክሽን ስራዎች ኮርፖራሽን መገንባቱ ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡
የማማከር እና የቁጥጥር ስራውን ያከናወነው ደግሞ የኢትዮጵያ ዲዛይንና ቁጥጥር ስራዎች ኮርፖራሽን ነው።
በተያያዘ የደቡብ እና ጋምቤላ ክልልን የሚያገናኘው የዚሁ የመንገድ ትስስር አካል የሆነው የሚዛን ዲማ የመንገድ ፕሮጀክትም በመጠናቀቅ ላይ ሲሆን፥ ፕሮጀክቱ 91 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመትን ይሸፍናል።
ለፕሮጀክቱ የሚውለውን 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የሚሸፈነው በኢትዮጵያ መንግስት መሆኑን የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታው የመንገድ ግንባታውን እያከናወነ የሚገኘው ኤም.ሲ.ሲ 17 የተባለ የቻይና አለማቀፍ የስራ ተቋራጭ ድርጅት መሆኑ ተገልጿል።
የማማከሩን ተግባር ደግሞ የህንዱ አርቪ አሶሲዬት ኮንሰልታንሲ ከኢትዮጵያው አማካሪ ድርጅት ኔት ጋር በጋራ እየሰሩ መሆኑን ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
Exit mobile version