አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1፤ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የምዕራብ አፍሪካዊቷን ሀገር ጋና ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ አዶ ሌላ የአራት ዓመት የስልጣን ጊዜ በማግኘት በድጋሚ ምርጫ ማሸነፋቸውን የምርጫ ኮሚሽኑ አስታውቋል ፡፡
የ 76 ዓመቱ አኩፎ አዶ 51ነጥብ 6 በመቶ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸውም ነው የተገለጸው።
ተቀናቃኛቸው እና የተቃዋሚ ናሽናል ዴሞክራቲክ ኮንግረስ መሪ ጆን ማሃማ 47 ነጥብ 4 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸውን የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ሃላፊ ጄን ሜንሳ አስታውቀዋል ፡፡
በመላ አገሪቱ በ 38 ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች በአጠቃላይ 17 ሚሊየን መራጮች መሳተፋቸው የተገለጸ ሲሆን ÷ መራጮችም ለብሔራዊ ፓርላማ 275 የሕግ አርቃቂዎችን መምረጣቸውም ተገልጿል ፡፡
በጋና የተካሄደውን አጠቃላይ ምርጫ የታዘቡ የአፍሪካ አህጉራዊ እና የምዕራብ አፍሪካ ክልላዊ ቀጠና ቡድኖች በምርጫው አካሄድ መርካታቸውን በመግለጫ አስታውቀዋል፡፡
በዚህም የምርጫ ታዛቢ ቡድኖቹ ኢኮዋስ ፣ አፍሪካ ህብረት እና የምዕራብ አፍሪካ የተባበሩት መንግስታት ጽህፈት ቤት በጋራ በሰጡት መግለጫ የጋና ህዝብ ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ በማከናወኑ አመስግነዋል ፡፡
ከዚያም ባለፈ ታዛቢ ቡድኖቹ ምርጫውን በበላይነት የሚከታተሉ የመንግስት ተቋማትም ሙያዊ እና ግልጸኝነት በተሞላበት መንገድ ሥራቸውን እንዲወጡ ማሳሰባቸው ተገልጿል ፡፡
ምንጭ፡- ሲጂቲኤን

