አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 10፣ 2013 (ኤፍቢሲ) በሊባኖስ ቆንስላ ጄኔራል አቶ ተመስገን ዑመር በትግራይ ክልል እየተካሄደ ስላለው ህግ የማስከበር፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ አፈፃፀም፣ የመልሶ ግንባታ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በተጨማሪም በሊባኖስ በቤት ሰራተኝነት እየሰሩ ስለሚገኙ ዜጎች ሁኔታም በዝርዝር አብራርተዋል፡፡
ቆንስላ ጄኔራል አቶ ተመስገን ዑመር ማብራሪያውን የሰጡት በሊባኖስ ተነባቢ ከሚባሉ ዘ ዴይሊይ ስታር ሊባነን እና ቢዝነስ ኢኮስ ከተሰኙ መገናኛ ብዙኀን ጋር ነው፡፡
በቆይታቸው ኢትዮጵያ ህግን ለማስከበር ባደረገችው ጥረት ያለማንም የውጭ ጣልቃ ገብነት በአጭር ጊዜ የተጠናቀቀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአሁን ወቅት መንግስት እያካሄደ ያለው ህገወጡ የህወሓት ቡድን ያፈራረሳቸውን መሰረተ ልማቶች መልሶ በመገንባት ላይ እንዳለና ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ እየተሰራ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡
በተጨማሪም ቆንስላ ጄኔራሉ መንግስት እያካሄደ ስላለው የህግ ማስከበርና የመልሶ ግንባታ ሁኔታ ለሊባኖስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጊዜያዊ ተጠሪ ለሆኑት ሃኒይ ኬማቴሊይ እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአፍሪካ፣ አሜሪካና እሲያ ጉዳዮች ዳሬክቶሬት ጀኔራል ለሆኑት ጂኦርጅ ጃላላ በስፋት ገለጻ አድርገዋል፡፡
በሊባኖስ በሚኖሩ ዜጎች ላይ እየደረሰ ስላለው የመብት ጥሰት እና በሚሲዮኑ በኩል እተደረጉ ስላሉ ጥረቶች አጽንዖት በመስጠት በዝርዝር አስረድተዋል፡፡
በሊባኖስ ከ2019 ጀምሮ በተከሰተው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ቀውስ ባሳደረው ተፅዕኖ በርካታ ዜጎች ለበለጠ ችግር ተጋላጭ መሆናቸውነ ገልፀዋል።
ይህን ተከትሎም ብዙ ዜጎች በአሰሪዎቻቸው በደል ስለሚደርስባቸው በየቀኑ ብዛት ያለቸው ዜጎች ወደ ቆንስላ ጽህፈት ቤት እየመጡ አቤቱታ እንደሚያሰሙ ቆንስል ጄኔራሉ አንስተዋል፡፡
አቤቱታ ከሚያቀርቡ ዜጎች መካከል አብዛኛዎቹ ደመውዛቸውን ከ1 ወር እስከ 5 ዓመት ድረስ ያልተከፈላቸው እንዳሉ ለመረዳት ተችሏል ብለዋል፡፡
ይህ ሁኔታ የሚያሳየው የሃገሪቱ የኢኮኖሚው መውደቅ ብቻ ሳይሆን ሃገሪቱ እየተከተለችው ያለው የአከፋፈል ስርዓት ዋንኛው መንስኤ መሆኑን ቆንስል ጄኔራሉ በቃለ ምልልሳቸው አውስተዋል፡፡
ቆንስላ ጄነራሉ በተለያየ ወቅት በመንግስት ወጪ ሰነድ አልባ ዜጎች ወደ ሃገራቸው የተመለሱ መሆናቸውን ገልጸው እነዚህ ዜጎች ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ድጋፍ እንዳደረጉም አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻም ክቡር ቆንስል ጄኔራሉ የቤት ሰራተኞች የመብት ጥሰትና እንግልት የሊባኖስን ገጽታ የሚያበላሽ ስለሆነ ሁሉም ሊባኖሳዊ ሃላፊነት ሊወስድ ይገባል ሲሉ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

