አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 13 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ከመከላከያ ሰራዊት በጡረታ የተገለሉ አባላትን በማሰባሰብና በመመልመል የትግራይ ልዩ ሃይልን እንዲቀላቀሉ ሲያደርጉ ነበሩ የተባሉ አራት የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት መኮንኖች ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡
ከአራቱ መካከል ከኮሎኔል ገብረመድህን ገብረመስቀል በስተቀር ቀሪዎቹ ከሰባት አመት በፊት በጡረታ የተገለሉ ሲሆኑ፥ ተጠርጣሪዎቹ ህገ መንግስቱን እና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በሃይል በመናድ ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ እየተከናወነባቸው ይገኛል፡፡
1ኛ ኮሎኔል ምሩፅ በርሄ፣ 2ኛ ኮሎኔል ገብረመድህን ገብረመስቀል፣ 3ኛ ኮሎኔል ተስፋዬ ሃጎስ እና 4ኛ ኮሎኔል መብራቱ ተድላ ናቸው፡፡
መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው 12 ቀናት ውስጥ የሰራቸውን በርካታ የምርመራ ስራዎች ለችሎቱ አብራርቷል፡፡
ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ ከሜጄር ጄኔራል ገብረመድህን ፍቃዴ (ወዲ ነጮ) ጋር በመሆን በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ኔትወርክ ግንኙነትን በማቋረጥ ተሳትፎ እንዳላቸው በሰው ምስክርና በቴክኒክ ምርመራ በማስረጃ አረጋግጫሁ ብሏል፡፡
የስምንት ሰዎችን የምስክርነት ቃል መቀበሉን የገለጸው መርማሪ ፖሊስ በትግራይ ክልል የፌደራል ፖሊስ አባላትና ተቋማት ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን ለይቶ በማስረጃ በማረጋገጥ ከመዝገቡ ጋር ማያያዙንም ጠቅሷል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው በመጥቀስ የወንጀል ተሳትፏቸው ተለይቶ አለመቅረቡን በማንሳት በነጻ አልያም በዋስ እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
መርማሪ ፖሊስም የእያንዳንዳቸውን ተሳትፎ ያብራራ ሲሆን በዚህም 1ኛ ተጠርጣሪ በሚሰሩበት የጥበቃ ስራ ላይ የራሳቸውን አባላት መልምለው በፌደራል ተቋማት ላይ ጥቃት ሊፈጽሙ እንደነበር በሰበሰብኩት ማስረጃ አረጋግጫለሁ ነው ያለው፡፡
እንዲሁም 2ኛ ተጠርጣሪ ሁለት ጊዜ በተሰማሩበት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ አባላትን አደራጅተው የትግራይ ልዩ ሃይልን እንዲቀላቀሉ ማድረጋቸውን ማስረጃ መሰብሰቡን ጠቅሶ፥ 3ኛ ተጠርጣሪም ወንጀሉ ሲፈጸም ህክምና ላይ ነበሩ ተብሎ በጠበቃቸው ለተነሳው መቃወሚያ መርማሪ ፖሊስ ወንጀሉ ሲፈጸም ብቻ ሳይሆን ለወንጀሉ መፈጸም ከሁለት አመት በፊት ጀምሮ ለፀረ ሰላም ቡድኖች መረጃ ሲያቀብሉ እንደነበርም ማስረጃ መሰብሰቡን አስረድቷል፡፡
4ኛ ተጠርጣሪም ቢሆኑ ከሜጄር ጀኔራል ገብረመድህን ጋር በመገናኘት ከመከላከያ በጡረታ የወጡ ሰዎችን በመሰብሰብ ለትግራይ ልዩ ሃይል አባላትን ሲመለምሉ እንደነበር ማስረጃ መሰብሰቡንም ነው ያስረዳው፡፡
ከዚህ ባለፈም በአዲስ አበባ ከተማ እያንዳንዳቸው ያደርጉት የነበረውን እንቅስቃሴ ማጣራቱንም ጠቅሷል፡፡
የሁለቱን ክርክር ያዳመጠው ችሎቱ ተጠርጣሪዎቹ የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብት እንዳላቸው ጠቅሶ መርማሪ ፖሊስ ምርመራውን በፍጥነት እንዲያከናውን ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ለተጨማሪ ምርመራም ለፖሊስ 10 ቀናትን ፈቅዷል፡፡
በታሪክ አዱኛ
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

