Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ መፋጠን እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 14 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽን እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ቡድን ሰሞኑን በፉሪ ሀና ሳይት እና በቦሌ አራብሳ ባደረገው የመስክ ምልከታ የ20/80 ኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ መፋጠን እንዳለበት አሳስቧል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ቡድን በፉሪ ሀና ሳይት የመስክ ምልከታ ባደረገበት ወቅት 49 ብሎኮች በግንባታ ላይ እንዳሉ እና አፈጻጸማቸው በአማካይ 87 በመቶ መድረሱን ከተቋራጮች ባገኘው መረጃ አረጋግጧል፡፡

በዚህ ፕሮጀክት የተቀናጀ የመሰረተ-ልማት ዝርጋታ እንዳልተጀመረ የተገለፀ ሲሆን፣ በአንጻሩ በግንባታ ሂደቱ ለ2 ሺህ 59 ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩ ተጠቁሟል፡፡

በፉሪ ሀና ሳይት በወሰን ማስከበር ችግር ምክንያት አምስት ብሎኮች እንዳልተገነቡ በፕሮጀክት ስድስት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የኮንትራት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደመላሽ ሙሉነህ ተናግረዋል።

የተጀመሩ ግንባታዎችን በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ ለማጠናቀቅ የሰሚንቶ አቅርቦት እና የዋጋ ግሽበት እንቅፋት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ለፕሮጀክቶች ግንባታ መጓተት ትልቁ ምክንያት የበጀት ችግር እንደሆነ የገለጹት አቶ ደመላሽ፣ በአሁኑ ወቅት የበጀት ችግሩ በመቀረፉ ባለፉት ስድስት ወራት ተቋርጦ የነበረው ግንባታ መጀመሩንም ነው የተናገሩት፡፡

በተመሳሳይም የቋሚ ኮሚቴው ቡድን በቦሌ አራብሳ ፕሮጀክት 12 እና 13 የመስክ ምልከታ ባደረገበት ወቅት በፕሮጀክት 12፣ 159 ብሎኮች እንዳሉ እና የግንባታ አፈጻጸማቸው 94 በመቶ መድረሱን በፕሮጀክት 13 ደግሞ 164 ብሎኮች እንደሚገኙ እና የግንባታ አፈጻጸማቸውም 93 በመቶ መድረሱን ከፕሮጀክት ሃላፊዎች ባገኘው መረጃ አረጋግጧል፡፡

በፕሮጀክት 12 የተቀናጀ የመሰረተ-ልማት ዝርጋታ ጅምሩ እንዳለ ያረጋገጠው ቡድኑ ከ3 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩ ማወቅ ተችሏል፡፡

በቀጣይ ሁለት ወራት ውስጥ ግንባታውን ለማጠናቀቅ እቅድ ቢያዝም፣ የሲሚንቶ ዋጋ ግሽበት እና የአቅርቦት ችግር የግንባታ ስራውን ሊያጓትተው እንደሚችል ስጋት መኖሩን የፕሮጀክት 12 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው ግርማ ተናግረዋል፡፡

የፕሮጀክት 13 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ቤተልሄም አድማሱ በበኩላቸው በወሰን ማስከበር እና በካሳ ክፍያ ምክንያት አምስት ብሎኮች ግንባታቸው በጅምር መቅረቱን ገልጸው፣ በሌላ በኩል 15 ብሎኮች በተጀመሩ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ግንባታቸው የተጠናቀቀ መሆኑን ለቋሚ ኮሚቴው መግለፃቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘኘው መረጃ ያመለክታል።

የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽን እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባልና የቡድኑ አስተባባሪ አቶ ታደሰ ወርዶፋ የፕሮጀክቶችን ግንባታ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ለማጠናቀቅ የወሰን ማስከበር፣ የመብራት መቆራረጥ፣ የበጀት እጥረት እና ተያያዥ ችግሮች በየደረጃው መፈታት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version