አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 14 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት የዜጎችን ደኅንነት ማረጋገጥ ቀዳሚው ተግባሩ አድርጎ መስራት እንደሚገባው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዛሬ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ትናንት ታኅሣሥ 13 ቀን 2013 ዓ.ም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ በኩጂ ቀበሌ ከሌሊቱ 10፡00 ሰዓት ላይ የታጠቁ ኃይሎች በእንቅልፍ ላይ በነበሩ ነዋሪዎች ላይ በለኮሱት እሳት እና በተኩስ ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል።
ይህ ተግባር በክልሉ ያለው የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ በከፍተኛ ሁኔታ እየተዳከመ መሄዱን ያሳያል ብሏል።
ኢሰመኮ የጥቃቱን ሂደት በተመለከተ ታኅሣሥ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ከሚመለከታቸው አካላት እና ከተጎጂዎች ጋር በመነጋገር ሲከታተልና ሲያጣራ ቆይቷል ነው ያለው።
በኩጂ ቀበሌ ከወረዳው መቀመጫ ከሆነችው ቡለን ከተማ 90 ሎ ሜትርበ ርቃ የምትገኝ ሲሆን የሺናሻ፣ የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች ይኖሩባታል ሲል ገልጿል።
ለቀበሌው የተመደበ የፖሊስ ወይም የፀጥታ ኃይል አለመኖሩን ኮሚሽኑ በክትትሉ መረዳቱን በመግለጫው አንስቷል።
ኮሚሽኑ ሁኔታውን እስካጣራበት ጊዜ ድረስ በቡለን ሆስፒታል 36 ተጎጂዎች እርዳታ እየተደረገላቸው ሲሆን አብዛኛዎቹ በጥይት ሌሎቹ በቀስት የቆሰሉ መሆናቸውን በምልከታ አረጋግጧል ነው ያለው።
በተጨማሪም ሰዎች ጥቃት የደረሰባቸውን ሁኔታ የሚያሳዩና የሚረብሹ የፎቶግራፍ ማስረጃዎች ለኮሚሽኑ ደርሰውታል፤ በሰው ሕይወት እና በአካል ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ የደረሱ ሰብሎችና የተሰበሰቡ ማሳዎች በእሳት ጋይተዋል ብሏል።
ቢያንስ 18 ያህል ነዶዎች ሲቃጠሉ ማየታቸውን አንድ ተጎጂ አስረድተዋልም ነው ያለው ኮሚሽኑ።
በጨላንቆ እና ዶሼ ቀበሌዎች ቤቶች እየተቃጠሉ እንደሆነ ከአካባቢው ለኮሚሽኑ የተላኩ መረጃዎች እንደሚያመላክቱም አንስቷል።
በድባጤ ወረዳ ዶንበን ቀበሌ ስጋት የገባቸው ነዋሪዎች ከታኅሣሥ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ቀያቸውን ጥለው እየተሰደዱ እንደሆነም ኮሚሽኑ ተረድቷል ሲል ገልጿል።
አካባቢውን በቅርበት እንዲጠብቅ የተመደበው ብሔራዊ የመከላከያ ሠራዊት ታኅሣሥ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ለማረጋጋት ተግባር ወደቦታው ተልከው የነበሩ አንድ የፌደራል እና ሁለት የክልሉ አመራሮችን ለማጀብ በሚል አካባቢውን ለቆ መሄዱ ታውቋል ብሏል።
ጥቃቱ የጀመረው ይህንኑ ተከትሎ እንደሆነና ሌሊቱን የጀመረው ጥቃት እስከ ቀኑ አጋማሽ ድረስ መዝለቁንም ለማወቅ ተችሏል ነው ያለው መግለጫው።
ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው ተጎጂዎች እንደሚሉት በጥቃቱ ከሞቱ ሰዎች መካከል አብዛኛው የሺናሻ ተወላጆች ናቸው ሲል አረጋግጧል ብሏል ኮሚሽኑ።
ከዚህ ቀደም በነበሩ ጥቃቶች ፈጻሚዎቹ ከ”ጫካ” የሚመጡ ሰዎች የነበሩ ቢሆንም፣ በዚህኛው ጥቃት “በስምና በመልክ የሚያውቋቸው”የበኩጂ ቀበሌ ነዋሪዎች ጭምር መሳተፋቸውን ከጥቃቱ የተረፉ ተጎጂዎች ገልጸዋል።
ኢሰመኮ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚከሰቱ ጥቃቶችን ተደጋጋሚነትና የክልሉን ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ሁኔታ አስመልክቶ፣ የፌደራሉንና የክልሉን መንግሥታት የተጠናከረ ትብብርና ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሻ ሲያሳስብ መቆየቱን በመግለጫው አንስቷል።
ጥቃቶቹ በመልክ እና በስፋት እየተባባሱ በመምጣታቸው ጉዳዩ አሁንም ትኩረት ይሻል ብሏል።
ስለሆነም በጥቃቱ ጉዳት ለደረሰባቸው እና ለተፈናቀሉ ሰዎች የህክምና እና ሰብአዊ እርዳታ እንዲቀርብ፣ እንዲሁም ተገቢው ማጣራትና ጥቃቱን ባለመከላከልም ሆነ በሌላ መልኩ ጥቃቱን የፈጸሙና ያባባሱ ሰዎችን ሕግ ፊት የማቅረቡ ሂደት ከወዲሁ እንዲጀመር ኮሚሽኑ አሳስቧል።
በአካባቢው የሚገኘውን የፀጥታ ኃይልና መዋቅር የሰዎችን ደኅንነት ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ በከፍተኛ ደረጃ በአፋጣኝ እንዲጠናከር ኢሰመኮ ጥሪ አቅርቧል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

