Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በህገ ወጥ መንገድ ወደ ውጭ ለመውጣት ሲዘጋጁ የነበሩ 45 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 15 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሃ ከተማ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ውጭ ለመውጣት ሲዘጋጁ የነበሩ 45 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።
የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የኮሙዩኒኬሽን ክፍል ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ወርቄ ጫኔ÷ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሁሉም ወጣት ሴቶች ናቸው ብለዋል።
በከተማዋ በሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ ተደብቀው ወደ ሱዳን ለመውጣት ሲዘጋጁ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት በተደረገ ክትትል መያዛቸውንም አስረድተዋል።
በተሳሳተ የህገ ወጥ ደላሎች ቅስቀሳ ከኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች ገንዘብ በመክፈል የመጡ መሆናቸውን ያመለከቱት ዋና ኢንስፔክተሩ፤ በዚህ ድርጊት የተሳተፉ አካላትን ለመቆጣጠር ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
አያይዘውም በህገ ወጥ መንገድ ከሃገር ለመውጣት ሲሞክሩ የተያዙትን ወጣት ሴቶች ወደ መጡበት ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እየጨመረ መምጣቱን የጠቆሙት ሃላፊዋ ÷ በተያዘው ዓመት ብቻ ከ150 በላይ ሴቶችና ህጻናትን በመያዝ ወደ መጡበት አካባቢ እንዲመለሱ መደረጉን አስታውሰዋል።
ወጣቶቹ ወደ ሱዳን ከገቡ በኋላ ወደ ዓረብ ሃገራት ለመሻገር አቅደው የነበረ ሲሆን ዓረብ ሃገር ከገቡ በኋላ 50 ሺህ ብር ለደላላ ተጨማሪ ክፍያ ለመፈጸም ተስማምተው ጉዞ መጀመራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version