አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፑሽኪን አደባባይ – ጎተራ ማሳለጫ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት 50 ከመቶ በላይ የግንባታ ስራ መጠናቀቁን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
የግንባታ ፕሮጀክቱን በተያዘው በጀት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑንም ባለስልጣኑ ገልጿል፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ እንደገለፁት÷ አሁን ላይ የዋሻ ቁፋሮ ስራን ጨምሮ ግንባታው በፍጥነት እየተከናወነ ነው፡፡
በመጭው ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ላይ ደግሞ ከቄራ ወደ ጎፋ ማዞሪያ የሚወስደውን የማሳለጫ ድልድይ ለማጠናቀቅ ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡
ይህ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት 3 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመትና ከ30 እስከ 45 ሜትር የሚደርስ የጎን ስፋት ያለው ሲሆን÷ የግንባታ ስራውን ቻይና ፈርስት ሀይ ዌይ ኢንጂነሪንግ የተባለ የስራ ተቋራጭ እያከናወነው ይገኛል፡፡
ቤስት አማካሪ ድርጅት ደግሞ የግንባታ ቁጥጥሩንና የማማከር ስራውን እያከናወነው ሲሆን ለግንባታውም ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ተመድቦለታል፡፡
የመንገድ ፕሮጀክቱ በሁለት በኩል 320 ሜትር ርዝመት ያለው ዋሻ፣ የፈጣን አውቶብስ መተላላፊያ መስመርን ጨምሮ ከስርና ከላይ 100 ሜትር ርዝመት ያለው ማሳለጫ እንዲሁም 6 ሜትር የሚረዝም የእግረኛ መንገድን አካቶ እየተገነባ መሆኑን ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

