አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 21 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በቂርቆስ፣ አራዳ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞች በ280 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነቡት የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) መሰረተ ልማቶች ተመረቁ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች በቂርቆስ የአይሲቲ መሰረተ ልማት ተገኝተው ጉብኝት አካሂደዋል።
በዚህ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻል እና የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ የዲጂታል ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶችን ማስፋፋት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
አያይዘውም ወቅቱ ዓለም በቴክኖሎጂ አንድ የሆነበት በመሆኑ በከተማዋም ደህንነቱ እና ጥራቱ የተጠበቀ ቴክኖሎጂ ማበልጸግ እና መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል።
የዲጂታል የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶች ተግባራዊ መሆን አገልግሎት ፈላጊውን አካል የጊዜ፣ የጉልበት እና እንግልት ከማስቀረቱም ባለፈ ሙስናን እና ብልሹ አሰራሮችን ለመከታተል ፋይዳው የጎላ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር አህመዲን አህመድ በበበኩላቸው፥ በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው የዲጂታል መሠረተ ልማት ዝርጋታ አበረታች መሆኑን እና ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ በኩል የተካሄደው የአይሲቲ መሰረተ ልማት ግንባታ ክፍለ ከተሞችን በማስተሳሰር የከተማዋን የአገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ እንደሚያደርግ ተጠቁሟል።
ከዚህ በፊት በአምስት ክፍለ ከተሞች የአይሲቲ መሰረተ ልማት ተገንብተው መመረቃቸውን ኢዜአ በዘገባው አስታውሷል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

