አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 22 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተቋሙ ዕቅድ አፈፃጸም፣ በኮርፖሬት ፋይናንስ አስተዳደር፣ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ግንባታ አፈጻፀም፣ በንብረት አያያዝ፣ አጠባበቅና አወጋገድ ዙሪያ የመስክ ምልከታ አድርጓል፡፡
በምልከታው የቡድኑ አባላት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም እና ከሌሎች የየዘርፉ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
የስትራቴጂክ ዕቅድና የአሊያንስ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ቡሴራ አወል አየር መንገዱ በኮቪድ ወረርሽን ሳቢያ ከበረራ ያገኝ የነበረው ገቢ ቢቀንስም የ25 አውሮፕላኖችን ወንበር በማንሳት ከሌሎች የጭነት አውሮፕላኖች ጋር የካርጎ አገልግሎት በመስጠት ከኪሣራ መዳን መቻሉን አንስተዋል፡፡
የዕቅድ አፈጻፀሙን በተመለከተም የውጭ በረራ የእቅዱን 85 በመቶ እንዲሁም የሀገር ውስጥ በረራ ደግሞ የእቅዱን 107 በመቶ መፈጸሙን አስረድተዋል፡፡
አያይዘውም የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተርሚናል 1 እና 2 ማስፋፊያ 96 በመቶ መዋቅራዊ ስራው መጠናቀቁን እንዲሁም የስካይ ላይት ሆቴል ማስፋፊያ በግንባታ ላይ መሆኑን ጠቅሰው የሰባት አውሮፕላን ማረፊያዎች ማለትም ሮቤ፣ ጅንካ፣ ኮምቦልቻ፣ ሽረ፣ ደምቢዶሎ፣ ነቀምት እና ጎዴ የመንገደኞች ማስተናገጃ ግንባታን ለማስጀመር ድርድር ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የሚዛን-አማን፣ ጎሬ-መቱ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ነገሌ ቦረናና ያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የኮሚቴው አስተባባሪ አቶ መስፍን መንገሻ አየር መንገዱ ከኮሮና ወረርሽኝ ተፅእኖ እና ኪሳራ ራሱን ለማትረፍ የወሰዳቸውን እርምጃዎች፣ ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነቱን ለማጎልበት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ በመንደፍና የተለያዩ የፋይናንስ ምንጮችን በማመቻቸት ዕቅዱን መተግበር እንደቻለ መናገራቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

