Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጃን ሜዳን ለጥምቀት በዓል ዝግጁ እንዲሆን ለተሳተፉ አካላት የምስጋና እና እውቅና መርሃ ግብር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 25፣ 2013(ኤፍ.ቢ.ሲ) ጃን ሜዳን ለጥምቀት በዓል ዝግጁ እንዲሆን ለተሳተፉ አካላት የምስጋና እና እውቅና መርሃ ግብር ተካሂዷል።
የዕውቅና እና የምስጋና መርሃ ግብሩን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት አዘጋጅቶታል።
በመርሃ ግብሩ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሃፊ እና የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ፣ የአዲስ አበባ እና የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጱዕ አቡነ መልከ ጸዲቅ፣ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ ፣ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ፣ የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ በላይ ደጀኔን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።
በመርሃ ግብሩ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ሀገረስ ብከት የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ዋና ሰብሳቢ ላዕከ ሄራን መንክር ግርማ የኮሮና ቫይረስ በሀገራችን መከሰቱን ተከትሎ መንግስት ፒያሳ የነበረው አትክልት ተራ ወደ ጃን ሜዳ እንዲዛወር መደረጉን አስታውሰዋል።
ጃን ሜዳን ለጥምቀት በዓል ዝግጁ ለማድረግም የአዲሰ አበባ ከተማ አስተዳደር በውስጥ የነበሩ የአትክልት እና ፍራፍሬ ነጋዴዎች ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወሩ ማድረጉን ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈም በስፍራው በዓሉን በተለመደ መልኩ ለማክበር እንዲቻል ከተማ አስተዳደሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር በተከታታይ እንዲጸዳ ማድረጉን ነው የገለጹት።
በአሁኑ ወቅትም ጃን ሜዳ የጥምቀት በዓልን በተለመደው መልኩ ማክበር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ጃን ሜዳ በዓሉን ለማክበር ዝግጁ እንዲሆን ላደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ፣የቤተክርስቲያን አባቶች ፣ የመዲናዋ ወጣቶች እና የተለያዩ እምነት ተከታዮች ምስጋና አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ እና የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጱዕ አቡነ መልከ ጸዲቅ በበኩላቸው÷ ከተማ አስተዳዳሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጃን ሜዳን ጽዱ ለማድረግ ያሳየውን ተነሳሽነት እና ትኩረት አድንቀው ይህ እንዲሆን ላደረጉት ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤም ምስጋና አቅርበዋል።
በሌላ በኩል ከተማ አስተዳደሩ እስካሁን ለቤተክርስቲያኗ ለጃን ሜዳ የይዞታ ማረጋገጫ ያልሰጠ በመሆኑ ለጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶ የይዞታ ማረጋገጫ በፍጥነት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
በመላኩ ገድፍ
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version