Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመዲናዋ ሲዘዋወር የነበረ 71 ካርቶን መድሐኒት መያዙን ፖሊስ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ በኮንትሮባንድ ሲዘዋወር የነበረ 71 ካርቶን መድሐኒት እና 57 ካርቶን ሽቶ መያዙን አስታወቀ፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ የተያዙት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ቦታው እፎይታ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ገደማ ፖሊስ ፍተሻና ቁጥጥር በሚያደርግበት ወቅት መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

አይሱዙ የጭነት መኪና ጨለማን ተገን በማድረግ 71 ካርቶን የህክምና መርፌ እና መድሃኒት እንዲሁም 57 ካርቶን ሽቶ በኮንትሮባንድ ጭኖ  ሲንቀሳቀስ እንደነበር የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ ቁጥጥር ዲቪዚዮን ኃላፊ ኮማንደር ትዕግስት ሃይሉ ተናግረዋል፡፡

በወቅቱ ፖሊስ ፍተሻ እያደረገ መሆኑን ያወቀው አሽከርካሪው መኪናውን አዙሮ በሌላ አቅጣጫ ሲጓዝ በጥርጣሬ በተደረገ ጥብቅ ክትትል በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ፊሊዶሮ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተሽከርካሪው ቆሞ መገኘቱን እና አሽከርካሪው ለጊዜው መሰወሩን ኮማንደር ትዕግስት ተናግረዋል፡፡

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ወንጀል መርማሪ ረዳት ኢንስፔክተር ካሚል አልዬ በበኩላቸው ተሽከርካሪው በፖሊስ መምሪያው ግቢ ቆሞ የሚገኝ ሲሆን የተያዙት መድሃኒት እና ሽቶዎች ለጉምሩክ ኮሚሽን ገቢ ይደረጋሉ ብለዋል፡፡

ተጠርጣሪውን በመያዝ ለህግ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡

የኮትሮባንድ ንግድ በህዝብና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ የሚያስከትል በመሆኑ ህብረተሰቡ ህገ- ወጥነትን በመከላከል እስከ አሁን እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጥሪውን ማቅረቡን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

Exit mobile version