Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በጣና ኃይቅ ከተስፋፋው የእምቦጭ አረም ከ85 በመቶ በላይ ተወግዷል – ኤጀንሲው

አዲስ አበባ ፣ ጥር 3 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በጣና ኃይቅ ላይ ተስፋፍቶ ከነበረው የእምቦጭ አረም ከ85 በመቶ በላይ መወገዱን የጣና እና ሌሎች የውሃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው የስርዓተ-ምህዳር ጥበቃና ልማት ባለሙያ አቶ ጤናው ምንውየለት ለኢዜአ እንደገለጹት የፌደራልና የክልሉ መንግስት በመቀናጀት ህብረተሰቡንና ሌሎች አጋሮችን በማሳተፍ ባደረጉት ጥረት አረሙን ማስወገድ ተችሏል።

በደቡብና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች በሚገኙ ስድስት የጣና ኃይቅ ዙሪያ ወረዳዎች ከ4 ሺህ 300 ሄክታር በላይ የሀይቁ አካልና ዙሪያ መሬት ላይ አረሙ ተስፋፍቶ እንደነበር አስታውሰዋል።

ጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን በተካሄደ ዘመቻ ከ3 ሺህ 759 ሄክታር ላይ አረሙን ማስወገድ እንደተቻለ አስታውቀዋል።

በዘመቻው በወረዳዎቹ አረሙ ከተስፋፋባቸው 30 ቀበሌዎች ውስጥ 25ቱ ሙሉ በሙሉ ነጻ መደረጋቸውን አመልክተዋል።

በጎንደር ዙሪያ ወረዳ በሶስት ቀበሌዎች አረሙን የማስወገድ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጹት ባለሙያው በደንቢያ ወረዳ ሁለት ቀበሌዎች ባለው የውሃ ጥልቀት እስካሁን አረሙን የማስወገድ ስራ አለመጀመሩን ተናግረዋል።

በህብረተሰቡ ተሳትፎ በዘመቻው የተወገደውን አረም በተከማቸበት ቦታ አድርቆ ለማቃጠል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

“በአንድ ወቅት ዘመቻ ብቻ በሀይቁ ላይ የተከሰተን አረም በዘላቂነት ማስወገድ አይቻልም” ያሉት ባለሙያው አረሙን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማጥፋት የተጀመረው ዘመቻ ሳይቋረጥ ለሶስት ተከታታይ አመት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመላክተዋል።

በእምቦጭ አረም ማስወገድ ዘመቻው 397 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን የገለጹት ባለሙያው አራት ማሽኖችም ጥቅም ላይ ውለዋል ነው ያሉት።

ለአረም ማስወገድ ስራው ከ61 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ባለሙያው አስታውቀዋል።

በጣና ኃይቅ ላይ የእምቦጭ አረም ከተከሰተ ከዘጠኝ ዓመት በላይ እንደሆነው ከኤጀንሲው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version