አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ 2011 ጀምሮ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂን ተግባራዊ እያደረገች መሆኗን የኢፌዴሪ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገለጹ።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ አባል ሃገራት የንጹህ ኃይል ሽግግርን በተመለከተ 26ኛ ጉባኤያቸውን አካሂደዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝን ጨምሮ የጉበኤው አባል ሃገራት የኢነርጂ ሚኒስትሮች በጉባኤው ተሳትፈዋል፡፡
የኢፌዴሪ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለም ኢትዮጵያን ወክለው በጉባኤው ላይ ንግግር አድርገዋል፡፡
ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግርም ኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ 2011 ጀምሮ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂን ተግባራዊ እያደረገች መሆኗን ገልጸዋል።
ሃገሪቱ አየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን አሉታዊ ውጤቶች ለመከላከል እና የካርበን ልቀትን ዜሮ ለማድረስ አልማ እየሰራች እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ለዚህም ምንም እንኳን ንጹህና ታዳሽ ኃይሎች ማጎልበቻ ኢንቨስትመንቶች በአንፃራዊነት ወጪያቸው ከፍተኛ ቢሆንም ኢትዮጵያ ለዚሁ የሚሆን ስትራቴጂ በመንደፍ የታዳሽ የኃይል ሀብቷን በኃላፊነት መንፈስ በማልማት ላይ ትገኛለችም ነው ያሉት ፡፡
በአሁኑ ወቅትም በጠቅላላው 8 ሺህ 370 ሜጋ ዋት ተጨማሪ ታዳሽ ሃይል ማመንጨት የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች በመንግስትና በግሉ ዘርፍ በስራ ላይ እንደሆኑ መናገራቸውን ከውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ኢትዮጵያ በኢነርጂው ዘርፍ እየተገበረች ያለው ሪፎርም ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ፣ አስተማማኝ፣ ቀጣይነት ያለው እና ዘመናዊ የኃይል አቅርቦት ተደራሽነትን በማረጋግጥ የ2030 ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የሚያስችላት በመሆኑ ከልማት አጋሮች ድጋፍ ትሻለች ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

