Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የደቡብ ክልል ምክር ቤት ከ616 ሚሊየን 843 ሺህ ብር በላይ ተጨማሪ በጀት አፀደቀ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 7 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ፣ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት ምክር ቤት እያካሄደ ባለው 5ኛ ዙር፣ 6ኛ አመት የስራ ዘመን 3ኛ አስቸኳይ ጉባኤ ከ616 ሚሊየን 843 ሺህ ብር በላይ ተጨማሪ በጀት እና የተለያዩ ሹመቶችን አፅድቋል፡፡
በጉባኤው መክፈቻ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሔለን ደበበ እንዳሉት በኢትዮጵያ የሚታዩ ግጭቶች እና የሕዝቦች መፈናቀልን በመዋጋት ረገድ ሁሉም ዜጋ ሊረባረብ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዝምድና መሥራት፣ በጥቅም መተሳሰር እና የሴራ ፖለቲካ በሕዝቦች አብሮነት ላይ ፈተና እየደቀኑ በመሆኑ ከወዲሁ ልንዋጋቸው ይገባል ያሉት ወይዘሮ ሔለን የውስጥ እና የውጭ ጠላቶችን ደባ በጋራ ሆነን መመከት አለብን ሲሉም ተናግረዋል።
ለዚህ ደግሞ ኅብረትን እና በጋራ መቆምን መለያችን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡
የክልሉ ምክር ቤት አባላት የቀጣዩ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍትሐዊ፣ ተዓማኒ እና ዴሞክሲያዊ እንዲሆን የድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
የክልሉ ምክር ቤት አባላት በህግ ማስከበር ዘመቻው ውድ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች የአንድ ደቂቃ የኅሊና ጸሎት አድርገዋል፡፡
ከምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ የተሰጠ ሲሆን ከፀጥታ ጋር በተያያዘም በክልሉ ሁከትና ትርምስ ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት እውን አይሆንም ሲሉ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው ምላሽ ሰጥተዋል ።
መንግስት የሴሮኞችን እኩይ ተግባር ለማክሸፍ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ቢገኝም ህዝቡ ይሔን ተገንዝቦ የሴሮኞችን ተግባር ከመንግሥት ጓን ቆሞ በበለጠ መስራት አለበት ብለዋል፡፡
ባለፋት ግዚያቶች የተከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት በተሰራው ስራ ለውጥ ቢኖርም የተቀረፈ ባለመሆኑ በቀጣይም አመራሩ ከህዝቡ ጋር በመሆን መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የፀጥታ ስራንም ሆነ ለሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች ሰላም መሠረታዊ ነገር ነው ያሉት አቶ እርስቱ ይርዳው ችግር በመፍጠር የተጠረጠሩ ግለሰቦች ተይዘው በህግ ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል ።
ከሀገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘም አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን አሳታፊ ማድረግ ስለሚያስፈልግ ለክልል ምክር ቤት አባላንትን ልዩ የምርጫ ክልሎችን በክልል ደረጃ ለመጨመር ታሳቢ ያደረገ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በተጨማሪ በጀት ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ 616 ሚሊየን 843 ሺህ ብር ለክልል ማዕከል ተጨማሪ በጀት አጽድቋል።
ከአስፈጻሚ አካላት ሹመትን በተመለከተ የምክር ቤት አባላት የነበሩና ሹመታቸውን ለማፅደቅ በወቅቱ በነበረው ወቅታዊ ችግር ሰባት የቢሮ ሀላፊዎች በተሰጣቸው ውክልና ሲያገለግሉ የነበሩ በምክትል ርዕሰ መስተደድር ማዕረግ ሲሰሩ የቆዩ አመራሮች ሹመታቸው ፀድቋል ።
በተጨማሪም ለክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር በመሆን ወይዘሮ ፈዲላ አደም እንዲሁም አቶ አለሙ ሀቹላ ምክትል ዋና ኦዲተር አቶ አባይነህ ሃቹላ በመሆን እንዲሾሙ በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በአቶ እርስቱ ይርዳው ቀርበው በምክር ቤቱ አባላት አስተያየት ከተሰጠ በኋላ ሹመታቸው መፅደቅ ችሏል ።
በመጨረሻም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለምክር ቤቱ ያቀረባቸውን ስድስት እጩ ዳኞችን በማቅረብ የፀደቀ ሲሆን ጥፋት የተገኘባቸው አንድ ዳኛም እንዲሰናበቱ በማድረግ ጉባኤውን አጠናቋል።
በብርሃኑ በጋሻው ተጨማሪ መረጃ ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version