Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመተከል ዞን ከህግ ማስከበሩ በተጓዳኝ  እርቅና አብሮነት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው – ግብረ ሃይሉ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 17፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በመተከል ዞን በሽፍቶች ላይ እየተወሰደ ካለው የህግ ማስከበር እርምጃ ጎን ለጎን እርቅና አብሮነት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን በመንግስት የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረሃይል አስታወቀ።

በዞኑ ከተፈቀደላቸው የጸጥታ ሃይሎች ውጭ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እንደማይፈቀድም ግብር ሃይሉ አስታውቋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የተደራጁ ሽፍቶች በተለያዩ ጊዜያት በፈጸሙት ጥቃት ዜጎች መገደላቸውና በርካታ ንብረት መውደሙ ይታወቃል።

የዞኑን ሰላም ለማስከበር በፌዴራል መንግስት የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ሃይል የአከባቢው ማህበረሰብ ጋር በመቀናጀት ዞኑን በማረጋጋት ላይ ይገኛል።

በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪና የግብረ ሃይሉ ማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ÷ ግብርሃይሉ ከሚወስደው የህግ ማስከበር እርምጃ ጎን ለጎን እርቅና አብሮነት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው ብለዋል።

በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄዱ ያሉ ህዝባዊ የውይይቶች ጥሩ ውጤት የተገኘባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በተከሰተው የጸጥታ ችግር ተደናግረውና በሽፍታው ተገደው ወደ ጫካ  ገብተው ከነበሩ የጉሙዝ ማህበረሰብ አባላት መካከል በርካታ እናቶች ሜዳ ላይ ለመውለድ ተገደዋል፤ ህጻናትም በችግር ውስጥ ይገኛሉ ብለዋል አቶ ተስፋዬ።

ሆኖም ግብረ ሃይሉ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ባደረገው ውይይትና የማህበረሰብ ሬዲዮ ጨምሮ በመጠቀም ወደየቀያቸው እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም እስካሁን ከ25 ሺህ በላይ የጉሙዝ ማህበረሰብ አባላት ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል።

ህገ-ወጥ ቡድኑ በንጹሃን ላይ በፈጸመው ዘግናኝ ድርጊት የጉሙዝም ሆነ የሌላው ማህበረሰብ  ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ህብረተሰቡ ከጥላቻና ቂም በመውጣት ሽፍታውን በጋራ መዋጋት እንዳለበት አሳስበዋል።

የግብረ ሃይሉን የጸጥታና ህግ ማስከበር ስራ የሚመሩት ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ በበኩላቸው ህብረተሰቡ በየአከባቢው ያሉ ወንጀለኞችን ለጸጥታ አካላት አሳልፎ በመስጠት የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

በንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃት ለመፈጸም የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በዞኑ ከተፈቀደላቸው የጸጥታ ሃይሎች ውጭ ማንኛውንም ዓይነት የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እንደማይቻልም አሳስበዋል።

ይህን ክልከላ ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ቡድን ላይ እርምጃ እንደሚወሰድም ነው ያስጠነቀቁት።

የአካባቢውን ሰላም ለማስተበቅና ወንጀለኞችን ለመቆጣጠር ሲባል የተቀመጠው የሰዓት እላፊ ገደብም በአግባቡ መከበር እንዳለበት ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

 

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version