አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በሳዑዲ ዓረቢያ በችግር ውስጥ የሚገኙ ከ34 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያንን ወደ አገር ቤት ለመመለስ መወሰኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።
በተሻሻለው ረቂቅ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መሰረት የዜጋ ዲፕሎማሲ አንኳር ጉዳይ ነው ብለዋል።
አቶ ደመቀ ይህንን የተናገሩት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር በነበራቸው የግማሸ ዓመት የዕቅድ አፈፃጸም ክንውን የጋራ ውይይት ላይ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው።
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ በመካከለኛው ምስራቅ በችግር ላይ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ በማድረግ በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ረገድ ሰፊ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
በዚሁ መሰረት ከሳዑዲ ዓረቢያ በአስቸኳይ መመለስ ያለባቸው ከ34 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን መለየታቸውን ገልጸው÷ በሣምንት አንድ ሺህ ዜጎችን ለማምጣት በተያዘው ዕቅድ መሰረት በቅርቡ መመለስ እንደሚጀምሩ ተናግረዋል።
‘በብልፅግና ዘመን የዜጋ ክብር ጉዳይ ማዕከላዊ ነጥብ ነው’ ያሉት አቶ ደመቀ÷ በተሻሻለው አዲሱ ረቂቅ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የዜጎች ክብር ትልቁ ትኩረት የተሰጠው ስለመሆኑ አንስተዋል።
ዜጎች ባሉባቸው አገሮች ችግር ሲገጥማቸው ለመመለስ፣ ስደት ከሄዱም በሕጋዊ መንገድ እንዲሆን በማድረግ ሕገወጥ ስደትን ለመከላከል የችግሩ ምንጭ ላይ ትኩረት ይደረጋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

