አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 19 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው 320 ሺህ 140 ሜትሪክ ቶን ምርት ማገበያየቱ አስታወቀ፡፡
ይህም ከግማሽ ዓመት ዕቅዱ ጋር ሲነፃፀር በመጠን 99 በመቶ እና በዋጋ 111 በመቶ ማሳካት መቻሉ ነው የተነገረው፡፡
ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር አምስት በመቶ የግብይት ቅናሽ በዋጋ ደግሞ የ13 በመቶ ጭማሪ አስመዝግቧል፡፡
ከዚህም ውስጥ 115 ሺህ ቶን ሰሊጥ ለማገበያየት ታቅዶ ከእቅዱ ከ122 በመቶ በላይ 140 ሺህ ቶን በማገበያየት የተሻለ አፈጻጸም ካላቸው ምርቶች መካከል አንዱ ሆኗል፡፡
ለግብርና ምርት አቀነባባሪዎች በተከፈተው ልዩ የግብይት መስኮትም 10 ሺህ 592 ቶን አኩሪ አተር በ198 ሚሊየን ብር አገበያይቷል፡፡
በዚህ ጊዜ ውስጥ ነጭ የርግብ አተር፣ ዥንጉርጉር ቦሎቄና ፒንቶ ቢን ወደ ዘመናዊ የግብይት መድረክ በመግባታቸው ምርት ገበያው የሚያገበያየው ምርት ብዛት 12 መድረሱ ነው የተነገረው።
ጥጥ፥ ቅመማ ቅመምና ጥራጥሬን ጨምሮ ዘጠኝ ተጨማሪ ምርቶችን ወደ ግብይት ለማስገባት የአዋጭነት ጥናት እየተካሄደ ነው ይገኛልም ተብሏል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ተቋማዊ አቅሙን በማሳደግና ተደራሽነቱን በማስፋት አራተኛውን የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከል በጎንደር ከተማ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚከፍት ተነግሯል።
የማዕከሉ መከፈት የዘመናዊ ግብይት ሥርዓቱን አገልግሎት ለአርሶ አደሩ፣ ለአቅራቢዎች፣ ለግብርና ምርት አቀነባባሪዎች፣ ለላኪዎችና ለሌሎችም አካላት የበለጠ ተደራሽ በማድረግ ካሉበት ሆነው ግብይት እንዲፈጽሙ ያስችላቸዋልም ነው የተባለው።
ምርት ገበያው ከዋናው መሥሪያ ቤት በተጨማሪ በሀዋሳ ፣ በሁመራና በነቀምት የኤሌክትሮኒክ የግብይት ማዕከላት ከፍቶ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
ተደራሽነቱን ይበልጥ ለማስፋት በአዳማና በጂማ የዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከላትን ግንባታ ያጠናቀቀ ሲሆን በሚዛን ተፈሪና በቴፒ አዳዲስ ቅርንጫፎችን ለመክፈት መዘጋጀቱን ተቋሙ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አስታውቋል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

